ዳሸን ባንክ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ቅርንጫፎችን ወደ ስምንት አሳደገ።

ዳሸን ባንክ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ተጨማሪ ቅርንጫፎችን በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞችም ከፍቷል።

ባንኩ በዛሬው ዕለት በቤተል አካባቢ ተቅዋ በሚል ስያሜ አዲስ ቅርንጫፉን አስመርቋል።

በተጨማሪ በአዲስ አበባ መርካቶ ጣና ገበያ ውስጥ አንዋር፣ በሀረር ከተማ አንሷር፣ በጅግጅጋ ጋራድ ዊልዋል፣ በጦራ ከተማ ጦራ የተሠኙ ተጨማሪ አዳዲስ ቅርንጫፎችን ለአግልግሎት ክፍት ማድረጉንም አስታውቋል።

ባንኩ ከዚህ ቀደም ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ በአዳማ ከተማ በረካ ፣ በድሬዳዋ ቡኻሪ ፣ በደሴ መሐመድ አል-አሙዲ የተሰኙ ቅርንጫፎችን ከፍቶ ለደንበኞቹ አገልግሎት በመስጠት ላይም ይገኛል ተብሏል።

በዚህም መሠረት በባንኩ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ አገልግሎት ብቻ የሚሰጡ የቅርንጫፎቹን ቁጥር ወደ ስምንት ያደረሰ ሲሆን ቅርንጫፎቹ ደንበኛውን ማዕከል ያደረገ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርገው የተደራጁ ናቸው ተብሏል፡፡

ባንኩ በዚህ የበጀት ዓመት ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ቅርንጫፎቹን ቁጥርም ወደ 12 ለማሳደግ ማቀዱንም ሰምተናል።

ሸሪክ የተሰኘው የዳሸን ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ተሠራጪተው በሚገኙ 423 ቅርንጫፎች በልዩ መስኮት እንዲሁም ስምንት በደረሱት ቅርንጫፎቹ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እንደሚሰጡም ተነግሯል።

ሸሪክ የሸሪዐህ የፋይናንስ መርሆችንና አሠራሮችን በመከተል በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ምንም ዓይነት ወለድ መክፈልም ሆነ መቀበል ላይ ያልተመሰረተ እንዲሁም ከመደበኛው የባንክ አሠራር ወይም ሒሳብ ጋር ሳይቀላቀል የሚሰጥ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ሲሆን ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ለደንበኞቹ ልዩ ልዩ የተቀማጭ ገንዘብ፣ የፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት ፣ የገቢና ወጪ ንግድ አገልግሎት፣ የገንዘብ ማስተላለፍ፣ የኤሌክትሮኒክ ባንኪግ እና ሌሎች የባንክ አገልግሎቶችን በአንድ ላይ አሟልቶ እየሰጠ እንደሚገኝም ተነግሯል።

የባንኩ ከወለድ ነፃ አገልግሎት በአውሮፓውያኑ መጋቢት 5 ቀን 2018 የተጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ175 ሺ በላይ ደንበኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል ተብሏል፡፡

በዚህ የአገልግሎት ጊዜ ውስጥ የባንኩ ተጠቃሚዎች የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 3 ቢሊየን ብር የደረሰ ሲሆን ባንኩ ከደንበኞቹ ለቀረቡለት የወለድ ነፃ የፋይናንስ ጥያቄዎች ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ መፍቀዱን ሰምተናል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በትግስት ዘላለም
መስከረም 22 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.