የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ባሰማራቸው የትራፊክ ስምሪት ባለሙያዎች በሚጠይቁት ጉቦ መማረራቸውን አስተያየታቸውን ለኢትዮ ኤፍ ኤም የሰጡ የታክሲ ሾፌሮች ተናገሩ።

በአዲስ አበባ የሚገኙ ታክሲ ስራ ላይ የተሰማሩ አሽከርካሪዎች ፣መንግስት ያውጣው የቅጣት እርከኑ የመንገድ ትራስፖርት ስምሪት ባለሙያዎች እንደልባቸው እንዲፈነጩብን እድል ሰጥቷቸዋል ብለውናል።

ሹፌሮቹ እንዳሉን ከሆነ ቀላል በሆኑ ጥፋቶች እየተከሰስን ነው፣ በጥቃቅን ጥፋቶች አንድ ሺህ እና ሁለት ሺህ ብር ነው እየተቀጣን ነው ብለዋል።

አዲሱ የስምሪት ስርዓተ ህግ የትራስፖር ስምሪት ባለሙያዎችን ተጠቃሚ ያደረገ ነው ፣ ትራፊክ መቶ ብር እና ሁለት መቶ ብር እየከሰሰ ለእነሱ በተለየ መንገድ እንዲቀጡ ህጉ መፍቀዱ ኞፌሮች ከስምሪት ባለሙያዎች ጋር እንዲደራደሩ ያስገድዳል ይህ መሆኑ ደግሞ ለስምሪት ባለሙያዎች እንዲያስፈራሩን እድል የሚሰጥ እና ለጉቦ ይዳርጋል ብለዋል።

የመንገድ ትራስፖርት ክስ ከአቅማችን በላይ ነው ፣አንድ ሺህ ብር ሁለት ሺህ ብር ተከሰን ከፍሉ ከምንባል ሙሉ ቀን ለምነን 300 ብር ጉቦ ብንከፍል ይሻላል ፣ ህጉ ለብልሹ አሰራር የሚገፋፋ ነው፣ እነሱም ህጉን ተገን አድርገው እኛን በሆነው ባልሆነው ያስፈራሩናል ሲሉም ሾፌሮቹ ቅሬታቸውን ነግረውናል፡፡

ሾፌሮቹ አክለውም የትራፊክ ፖሊስ ቅጣት ሚዛናዊ እና ተገቢው ነው የመንገድ ትራስፖርት እንደዛው ተመጣጣኝ ክስ ቢሆን አሸከርካሪም አይጎዳም መንግስትም ተገቢውን ገቢ ያገኛል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበበ ትራስፖርት ቢሮ የስነ ምግባር እና የፀረ ሙስና ዳይሬክተሩ አቶ አምባላይ ዘራይ የኮቪድ 19 ወረርሺኝን ተከትሎ የቅጣት ማሻሻያዎች ተደርጓል ነገር ግን ህጉ ለመንገድ ትራስፖርት ስምሪት ባለሙያዎች ያደላነው መባሉ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

በእንደዚህ አይነት ጉዳይ ላይ መረዳዳት ያለብን እና የመጀመሪያው ጥያቄ መሆን ያለበት ለምን ያጠፋሉ? የሚለው እና አጥፍተው ህጉ ለእነሱ ያደላ ነው ማለት ምን አይነት አመክንዮ ነው? በሚል ጥያቄውን በጥያቄ መልሰዋል አቶ አምባላይ ፡፡

ሌብነት እና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት መሰራት ያለበት በጋራ ነው አሽከርካሪውም ሆነ የስምሪት ባለሙያዎች መገዛት ያለባቸው ለህግ እና ስርዓት መሆን አለበት ሲሉም ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በዳንኤል መላኩ፡፡
ጥቅምት 4 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *