የፌደራል መንግስት የበጀት ድጎማ ቢቀር እዉን ትግራይ ክልል ተጎጂ ናት

በፌደራልና በትግራይ ክልል መንግስት መካከል ያለዉ ግንኙነት መሻከር ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡

ግንኙነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባብሶ አሁን ላይ የድጎማ በጀትን ለክልሉ መንግስት በቀጥታ አልሰጥም የሚል ዉሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሆነ ፓርላማው 6ኛዉን ሀገራዊ ምርጫ በሕገ መንግሥት ትርጓሜ እንዲራዘም ሲወስን የትግራይ ክልል መንግስት ደግሞ አይ የህገ መንግስት አሰራር መጠበቅ አለበት የሚል ክርክር አንስቶ ምርጫዉን አደረገ፡፡በምርጫዉም ቀድሞም ክልሉን ሲያስተዳድር የነበረዉ ህወሃት አሸነፍኩ ብሎ ቀጠለ፤የምርጫዉ ጉዳይ የክልሉ መንግስት ከፌደራል መንግስት ጋር የነበረዉን ግንኙነት ይበልጥ እንዲሻክር አደረገዉ፡፡

አሁን ላይ አንዱ አንዱን ኢ-ህገ መንግስታዊ ነዉ እያለ መወነጃጀሉ ቀጥሏል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌደራል መንግሥት ከትግራይ ክልል መንግስት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳያደርግ ውሳኔ ማሳለፋን ተከትሎ የገንዘብ ሚንስቴርም በክልሉ የሚገኙ የካቢኔ አባላት ህጋዊ ባልሆነ ምርጫ ተመርጠናል በሚል የሀገሪቱን ህገ መንግስት በመጣሳቸው አሁን ባለው ሁኔታ ለትግራይ ክልል መንግስት በጀት እንደማይለቅ አስታዉቋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤምም ይህ ጉዳይ በፌደራልና በትግራይ ክልል በተናጠል፤እንደ አጠቃላይ ደግሞ እንደ ሃገር ምን አይነት ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል ሲል የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን ጠይቋል፡፡

አቶ አማን ይሁን ረዳ የኢኮኖሚና ቢዝነስ ጉዳዮች ተንታኝ ናቸዉ፡፡

እርሳቸዉ እንደሚሉት፣የፌደራል መንግስቱ በትግራይ ክልል ከሚገኙ የወረዳና ከተማ አስተዳደሮች በኩል በተጠና ሁኔታ እንዲደርሳቸው ጥረት ይደረጋል ማለቱ በራሱ የህጋዊነት ጥያቄ አለበት ይላሉ፡፡

ምክንያቱ ደግሞ አሁን ባለዉ አሰራር ፌደራል መንግስት ከክልል መንግስታት፣የክልሎች ደግሞ ከዞንና ወረዳዎች ጋር እንጂ የፌደራል መንግስት በቀጥታና በተናጠል ከዞንና ወረዳዎች ጋር ግንኙነት ፈጥሮ የሚሰራበት አሰራር አለመኖሩን ይጠቅሳሉ፡፡

ይህን የህግ ክፍተት እንዳለ ይዘን የድጎማ በጀቱን ጉዳይ ብናነሳም የክልሉን መንግስት ብዙም የሚያስጨንቅ ላይሆን ይችላል ይላሉ፡፡

ለማሳያነትም ቀደም ሲል ያሉትን አሰራሮች ብቻ ብንመለከት ትግራይ ከ10 ቢሊዮን ብር ብዙም ያልበለጠ በጀት ይመደብለታል፤በአንጻሩ የፌደራል መንግስት በትግራይ ካሉ የተለያዩ ድርጅቶች በግብር መልክ እስከ 9 ቢሊዮን ብር ይሰበስባል፡፡እናም የክልሉ መንግስት በቀጣይ የሰበሰብኩትን ግብር ለፌደራል መንግስት አልክም ቢል የሚያጣዉ ከአንድ ቢሊዮን ብር ብዙም ከፍ ያላለ መሆኑን የኢኮኖሚ ባለሙያዉ ይጠቅሳሉ፡፡

ለወረዳዎችና ዞኖች የሚላክ ከሆነ ደግሞ ክልሉን ምንም አጣብቂኝ ዉስጥ የሚከተዉ ነገር አይኖርም ነዉ የሚሉት፡፡

ከዚህ ይልቅ እንደ ሃገር የሚያሳድረዉ ተጽዕኖ ያመዝናል የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያዉ በትግራይ ክልልና በፌደራል መንግስት መካከል ያለዉ ዉጥረት በዚህ መልኩ ከቀጠለ አንድ የሰላም እጦት ማሳያ ተደርጎ ስለሚወሰድ ሀገራዊ ንግድና ኢንቨስትመንቶች እንዲቀዛቀዙ ሊያደርግ ይችላል፤የሸቀጦችና ምርቶች ዝዉዉር እንዲስተጓጎል ምክንያት ሊሆን ይችላል፤ይህ ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚያመጣዉ ተጽዕኖ ያመዘነ እንዲሆን ያደርገዋል ነዉ የሚሉት፡፡

የኢንቨስትመንት አማካሪ የሆኑት አቶ ያሬድ ሃይለ-መስቀል ደግሞ በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚኖረዉን ኢኮኖሚያዊ ጫና በተመለከተ የአቶ አማን ይሁንን ሃሳብ ይጋሩና የትግራይ ክልልን በተመለከተ ግን የተለየ ሃሳብ ያነሳሉ፡፡

አቶ ያሬድ እንደሚሉት የበጀት ድጎማዉ በሰዓቱ ተለቆ ለታለመለት ዓላማ መዋል ካልቻለ በተለይም በክልሉ በፌደራል መንግስት የተያዙ ጅምር ፕሮጀክቶች፣ መሰረተ ልማቶችና የተለያየ ድጎማ የሚደረግላቸዉ ስራዎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል፤ፕሮጀክቶች ሊቆሙ፣በዚህም የተሰማሩ ሰራተኞችና ጥቅም የሚያገኙ ሰዎች ተጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ በሂደትም ተጽዕኖዉ ወደ ህብረተሰቡ መድረሱ አይቀርም ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡

አቶ አማን ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለዉን ሁኔታ ስንመለከት፣አለማቀፋዊ የሆኑ ወንጀሎች ሲሰሩ፣የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጠሩ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦች ይጣላሉ፤በኢትዮጵያ ያለዉ ግን የፓርቲዎች ጠብ ነዉ፣ይህን መሰል እርምጃ መዉሰድ ላይ አያደርስም የሚል ሃሳብም አላቸዉ፡፡

አቶ ያሬድም ቢሆኑ ያጠፋዉ አካል ድርጅትም ይሁን ግለሰብ ተለይቶ ነዉ ማዕቀብ የሚጣለዉ እንጂ አጠፋ የተባሉት ፖለቲከኞች እንደ ፈለጉ ተለቀዉ ሌላዉን ህብረተሰብ ሊጎዳ የሚችል ዉሳኔ ማሳለፍ ተገቢ አይደለም ይላሉ፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹ ምክረ-ሃሳባቸዉን ሲሰነዝሩም፤ልዩነቶች የቱንም ያህል የሰፋ ቢመስሉም ተቀራርቦ መነጋገር ከተቻለ መፍትሄ ይኖራልና ወደ ዉይይትና ድርድር ሊመለሱ ይገባል፤በፓርቲዎች እልህ ምንም የማይመለከተዉና ለፍቶ አዳሪዉ የህብረተሰብ ክፍል ተጎጂ መሆን የለበትም ይላሉ፡፡

ከዚህ ባሻገር በፓርቲዎች መካከል በተፈጠረ ክፍተት ሌሎች የሃገሪቷን ሰላም የማይፈልጉ የዉጭ ሃይሎች ገብተዉ ሀገሪቷ ከማትወጣዉ ችግር ዉስጥ እንዳይጨምሯት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፤ይህ ፓርቲዎችንም የታሪክ ተወቃሽ የሚያደርጋቸዉ መሆኑን መገንዘብ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በሙሉቀን አሰፋ
ጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.