የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በተከሰተ አለመረጋጋት ለወደሙ ኢንቨስትመንቶች ካሳ መስጠቱን የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

ከወራት በፊት በክልሉ በተስተዋለው ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ከተሞች መካከል ሻሸመኔ ፤ ዝዋይ ጅማ እና ሌሎች መሰል ከተሞች የሚገኙ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት እንደደረሰ ይታወቃል፡፡

በዚህ ውድመት ምክንያትም ባለሃብቶች ንብረቶቻቸውን ባንድ ጀንበር አጥተዋል በርካቶችም ከስራቸው ተሰናብተዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም ከደረሰው የንብረት ውድመት ጋር በተያያዘ የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑ ባለሀብቶች እየተከናወነ ስለሚገኝ ድጋፍ ጠይቋል፡፡

በክልሉ ካሉት ከ12 ሺህ በላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ውስጥ 89ኙ ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ወድመዋል።

የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዋሲሁን ጎልጋ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት ቀደም ሲል በክልሉ የተፈጠሩ የፀጥታ ሁኔታዎች ለኢንቨስትመንት ፍሰቱ ስጋት እንዳይሆኑ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡

በተለይም የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ፕሮጀክቶችን በመለየት ተግባራት በመለየት ዝርዝራቸውን ማስተላለፈ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

በክልሉ በተፈጠሩ አለመረጋጋቶች የወደሙ ኢንቨስትመንቶችን መልሶ ከማቋቋም አኳያ ኮሚሽኑ ምን ምን ተግባራትን አከናወነ ሲል ኢትዮ ኤፍ ኤም አቶ ምክትል ኮሚሽነሩን ጠይቋል፡፡

አቶ ዋሲሁን እንደሚሉት ንብረታቸው የተቃጠለባቸው ባለሃብቶች ከቀረጥ ነፃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻል የማበረታቻ ድጋፍ እንዲያገኙ ተመቻችቶላቸዋል ብለዋል፡፡

እድሉ አንዴ ብቻ የሚሰጥ ሲሆን እንደዚህ አይነት አደጋዎች ሲከሰቱ በዚህ ደረጃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አቅጣጫ ተቀምጧል በማለት አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የባንክ ብድር ያለባቸው ከሆኑም የፎይታ ጊዜ እንዲሰጣቸው በፌደራል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኩል አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።

በሌላ መልኩ ባለሀብቶቹ ከዚህ ኛለን የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ አልያም ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ጥያቄ ካላቸው እንዲስተናገዱም ተወስኗል ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ከተፈጠሩ የፅጥታ ችግሮች ጋር በተገናኘ ስጋት ካለባቸውም የቦታ ለውጥ ጥያቄም ካቀረቡ በልዩ ሁኔታ የሚስተናገዱበትን አሰራር ዘርግተን ባለሀብቶችን እያስተናገድን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በማሳያነት ከ250 እስከ 300 ሚሊየን የንብረት ውድመት ያጋጠመው ሼር ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ እንዲገባ ተደርጓል ሲሉ አቶ ዋሲሁን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ከ16 ሺህ በላይ የሚሆኑ ስራ አጥ ዜጎች በተደረገው ድጋፍ መሰረት ወደ ስራ ተመልሰዋል ብለዋል፡፡

ሀላፊው እንደሚሉት የአካባቢውን ዜጎች ለጥቃት የሚያነሳሱ ገፊ ምክንያቶች ውስጥ የኦሮሚያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን የልማት መሬቶችን ሲሰጥ ከካሳ ጀምሮ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ከማረግ አኳያ ውስንነቶች እንደነበሩ ያነሳሉ፡፡

በክልሉ የሚተገበሩ ኢንቨስትመንቶች ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመቆራኘት ዜጎችም የባለሀብቱን ንብረት እንደራሳቸው እንዲያዩ የሚያስችል እምነት ማሳደግ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡

በሌላ መልኩ የክልሉ መንግስትም የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ሀላፊነቱን ይወጣል ያሉት ም/ል ኮሚሽነሩ ባለሀብቱ የዘረጋውን የኢንቨስትመንት ካፒታል የሚመጥን የደህንነት አጠባበቅ ስርዓትን አካታች ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡

ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ኢንቨስትመንት እንዲቀዛቀዝና ስጋት እንዲኖር የተደረገውን እኩይ ተግባር በመቀልበስ የክትትል እና ድጋፍ ስራዎች በመሰራታቸው ኢንቨስትመንቱ ተመልሶ እንዲመጣ ማድረግ መቻሉን የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

በቀጣይም በክልሉ የኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ለሚሰማሩ ዜጎች ኮሚሽኑ በሩ ክፍት መሆኑን አቶ ዋሲሁን ገልፀዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በ 2012 ዓ.ም 2ሺህ 400 ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ስራ ለመግባት እንቅስቃሴ ከጀመሩት ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወደ ተግባር መግባታቸውን ከክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

በተጨማሪም ባሳለፍነው ክረምት በነበረው ከባድ ጎርፍ ምክንያት ለወደሙ የአበባ እና አትክልት እርሻ ኢንቨስትመንቶች ካሳ ለመክፈል ጥናት መጀመሩን ገልጿል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በደረሰ አማረ
ጥቅምት 10 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.