ፕሬዘዳንት ትራምፕ ኮሮና ቫይረስ አሜሪካንን እንዲያዋርድ እድል ሰጥተውታል ሲሉ ጆ ባይደን ተናገሩ።

አሜሪካንን ለቀጣዮቹ አራት አመታት ለመምራት በምረጡኝ ቅስቀሳ የተጠመዱት ትራምፕና ባይደን ትናንት የመጨረሻ ክርክራቸዉን አድርገዋል፡፡

በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ትራምፕና ባይደን በትናንትናዉ እለት ምሽት ላይ ባደረጉት ክርክርም ትራምፕ በርከት ያሉ ትችቶችን አስተናግደዋል፡፡

ከዚህ ዉስጥም የኮሮና ቫይረስ ጉዳይ ትራምፕን ለትችት ከዳረጋቸዉ ጉዳዮች አንዱ ሆኗል፡፡

ጆ ባይደን፣የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ሌሎች ሀገራት ትኩረት ሰጥተዉና የተለያዩ መከላከያ መንገዶችን ተጠቅመዉ ስርጭቱን መግታት ሲችሉ ትራምፕ ግን ገና ከጅምሩ ቀለል አድርገዉ መመልከታቸዉ የተቀረዉ የህብረተሰብ ክፍልም እንዲዘናጋ አድርገዋል፤ከዛ በኋላም ቢሆን አስተዳደራቸዉ መቆጣጠር አልቻለም፤ይህ ደግሞ ታላቋን ሀገር አሳፍሯታል ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም አሜሪካ የሁሉም ዜጎቿ ሆና ሳለ የነጭ የበላይነትን በማቀንቀን ይህ ደግሞ በምላሹ በሃገሪቱ የተለያዩ ቀዉሶች እንዲፈጠሩ አድርጓል፤ይህን አይነት መሪ አሜሪካ አያስፈልጋትም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ትራምፕ በበኩላቸዉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸዉን ገልጸዉ ይህ ባይሆን ኖሮ ጉዳቱ ከዚህም የከፋ ሊሆን ይችል እንደነበር አብራርተዋል፡፡

ዘረኝነትን በተመለከተ እንዳዉም የእሳቸዉ ስም ከዚህ ድርጊት ጋር ተያይዞ መጠቀሱ እንደሚያስገርማቸዉና ይህን የሚሉት አካላትም እርሳቸዉን ካለመረገዳት ወይም ሆን ብለዉ ለፖለቲካ አላማ ካልሆነ በስተቀር ዘረኝነትን ከሚያቀነቅኑ ሰዎች እኔ ትኩረት የማልሰጠዉና የመጨረሻዉ ሰዉ ነኝ ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ከዚህ ባሻገርም በምርጫ ወቅት በሃገሪቱ ስለሚታየዉ የዉጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት፣የአየር ንብረት ለዉጥና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ ክርክሮችን አድርገዋል፡፡

12 ቀናት ብቻ በቀሩት የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ፣አሁንም የምረጡኝ ቀስቀሳዉ ተጧጡፎ የቀጠለ ሲሆን የቀድሞዉ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ አሜሪካዊያን ድምጻቸዉን ለባይደን እንዲሰጡ መጠየቃቸዉ የሚታወስ ነዉ፡፡

ኦባማ በንግግራቸዉ ጆ ባይደን ቢመረጡ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልም ሆነ ሃገሪቱ ወደ ኋላ ያለችበትን የአየር ንብረት ለዉጥን የመከላከሉ ጉዳይ በትኩረት እንደሚሰሩና ለስራ አጥ አሜሪካዊያንም ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥር አማራጭ እንዳላቸዉ ኦባማ እምነታቸዉን ገልጸዋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በሙሉቀን አሰፋ
ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *