በወላይታ ዞን ቦዲቲ ከተማ ባሳለፍነው ቅዳሜ ሌሊት የተፈጸመው ምንድን ነው?

በወላይታ ዞን ቦዲቲ ከተማ የታጠቁ ዘራፊ ቡድኖችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተንቀሳቀሱ የጸጥታ ሀይሎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

ባሳለፍነው ቅዳሜ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ገደማ የታጠቁ ሁለት የዘራፊዎች ቡድን በቁጥጥር ስር ለማዋል ተንቀሳቅሰው የነበሩ የጸጥታ አካላት የመኪና አደጋ ደርሶባቸዋል ተብሏል፡፡

የደቡብ ክልል የሰላምና የጸጥታ ቢሮ ምክትል ሀላፊ እና የግጭት መከላከል እና አፈታት ዘርፍ ሀላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት በእለቱ በወላይታ ዞን ቦዲቲ ከተማ የታጠቁ ዘራፊዎች ቡድን መኪና በማስቆም ዝርፊያ እየፈጸሙ መሆኑን ጥቆማ የደረሰው የአከባቢው መደበኛ የፖሊስ ሀይል በዘራፊዎቹ ጥቃት ተፈጽሞበታል፡፡
በኃላም በአከባቢው የነበረ የፌደራል የፀጥታ ሀይል በስፍራው ደርሶ የተወሰኑት በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡

በተመሳሳይ ሰአት በዚህችው ከተማ ሌላ ዝርፊያ ላይ የነበሩትን የዘራፊ ቡድን ለመያዝ ሲሞክር የዘራፊ ቡድኑ አንድ አባል ለማምለጥ ሲሞክር በመኪና ተገጭቶ ወዲያው ህይወቱ አልፏል፡፡

ያመለጡትን ለመያዝ በነበረ ጥረት ወቅት ግን የጸጥታ አካላቱን እና የመጀመሪያ ተጠርጣሪዎችን ይዞ የነበረው መኪና ተገልብጦ በአንድ የጸጥታ ሀይል ላይ የሞት አደጋ ሲከሰት አምስቱ ላይ ጎዳት ደርሶባቸው በህክምና ላይ ይገኛሉ ብለውናል፡፡

ከተያዙት ተጠርጣሪዎች ውስጥ ሁለቱ በሆስፒታል ህክምና ላይ እንዳሉ ህይወታቸው ማለፉን አቶ አንድነት ጨምረው ይናገራሉ፡፡

አሁን በአከባቢው ምንም አይነት ችግር የለም ነው ያሉት አቶ አንድነት፡፡

በክልሉ ቁጥሩ እየጨመረ የመጣውን የዝርፊያ ወንጀል ለመከላከል የአከባቢዎቹ ሚሊሻና የክልሉ ልዩ ሀይል በጋራ እየሰሩ መሆኑንም ነግረውናል፡፡

እርሳቸው ይህንን ይበሉ እንጂ ኤትዮ ኤፍ ኤም ያናገራቸው የቦዲቲ ከተማ ነዋሪዎች ነገሩ እንደተባለው ዝርፊያ እንዳልሆነ፤ሞተ የተባለው ወጣትም በቅርቡ ከዩቨርስቲ የተመረቀ ወጣት መሆኑን እና እኔን አታውቁኝም ወይ እያለ ሲማጸን እንደነበር ሰምተናል ብለውናል፡፡

ተገለበጠ የተባለው መኪናም ከከተማው ወጣ ባለ ቦታ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎች ችግሩ የተከሰተውም እና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ሆስፒታል የደረሱበት ሰአት ከሌሊቱ 7 ሰዓት ሳይሆን 4፡30 እንደሆነ ነው ለጣቢያችን የተናገሩት፡።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በከተማዋ እና አከባቢው ከፍተኛ የጸጥታ ቁጥጥር እየጨመረ መሆኑንም ከነዋሪዎቹ ሰምተናል፡፡

በያይኔአበባ ሻምበል
ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *