በኢትዮጵያ ብሔርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ለምን ቀጠሉ?

ኢትዮጵያ በለውጥ መስመር ላይ ናት ከተባለ 3 አመት ሊሞላ ጥቂት ወራት ቀርቷል፡፡

ታዲያ የለውጥ ሀይሉ ስልጣን በያዘ በጥቂት ወራት ውስጥ በኢትዮጵያ ማንነቶችን መሰረት ባደረጉ ጥቃቶች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀል እና መሞት የተለመደ ዜና ሆኗል።

ብሔር ተኮር ጥቃትና ግጭት ወደ ሥልጣን ከመጡ ሶስት አመት ሊሆናቸው ጥቂት ወራት ለቀራቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና መንግስታቸው ከጅምሩ ፈተና እንደሆነባቸውም ብዙዎቹ ይናገራሉ፡፡

ባለፉት 2 አመታት ብቻ በአብዛኞቹ ክልሎች ግጭት ተከስቷል ፣ እነዚህም ግጭቶች አብዛኞቹ ብሔር ተኮር ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ በግጦሽ መሬት፣ በወሰን አስተዳደር እና መሰል ምንያቶች የተነሱ ናቸው፡፡

ታዲያ የለውጥ ሐይሉ መንግስት ሆኖ ሀገር ማስተዳደር ከጀመረ ገና 6 ወራት ሳይሞላው ፣ በሶማሊ ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፣በደቡብ ክልል ጌድዮና በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ፣በሐዋሳ እና ወላይታ የጉራጌና ቀቤና ብሔረሰቦች ፣ በአማራ ክልሎች ፣በብሔር ተኮር ጥቃት የበርካታ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ህይወት አልፏል።

በሀገሪቱ በየጊዜው እዚህም እዚያም ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች ይነሳሉ በተለይ በኦሮሚያ ክልል የሚነሱ ብሄር ተኮር ግጭቶች ግን አሁንም መቋጫ አላገኙም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በተለይም ከአማራ ክልል ውጪ በሚኖሩ የአማራ ብሔር ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ተሰንዝረው የበርካቶች ህይወት ጠፍቷል፣ንብረታቸው ወድሟል ከትውልድ ቀዬአቸውም ተፈናቅለዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም ይህ ለምን ሆነ? ማነው ከጥቃቱ ጀርባ ያለው? ፍላጎታቸውስ ምን ይሆን? ሲል ከፖለቲከኛው አማንይሁን ረዳ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አቶ አማንይሁን እንዳሉት ኢትዮጵያ አሁን ባለው የለውጥ ሂደት ውስጥ ለውጡ ከላይኛው እስከ ታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ስር ባለመስደዱ ጥቅማቸው የተነካባቸው እና በህግ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉ ቡድኖች እና ግለሰቦች የህግ የበላይነት እንዳይከበር የቻሉትን ያህል እያደረጉ ነው ብለዋል።

ተስፋ አድርገውት የነበረው የኢኮኖሚ እና የስልጣን ጥቅም የቀረባቸው ሐይሎች ደግሞ መንግስትን እረፍት በመንሳት የህዝብ ቁጣ እንዲበረታበት በማድረግ እና ፋታ በመንሳት ወደ ድርድር እንዲመጣ ማድረግ ነው አላማቸው ይላሉ አቶ አማን ይሁን፡፡

ሌላኛው ደግሞ ዲሞክራሲያዊ እና ታአማኒ የሆነ ምርጫ ቢካሄድ ስልጣን አላገኝም የሚል እና በግርግር ስልጣን መያዝ የሚፈልገው ቡድን ከጥቃቶቹ ጀርባ መኖሩንም ፖለቲከኛው ይናገራሉ፡፡

ያለ ችሎታቸው ፣ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነትና ተአማኒነት የሌላቸው በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙትም ብሔር ተኮር ጥቃትና ግጭት እንዲስፋፋ የሚሰሩ መኖራቸውንም አቶ አማን ይሁን ይገልፃሉ፡፡

እንደ ሀገር የተገባበት ለውጥ ከባድ ፣ ፈታኝ ፣ አቅም የሚጠይቅ እና የተረባረበ ሐይል የሚያስፈልገው መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ሊረዳ እንደሚገባም ፖለቲከኛው ተናገረዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶች እንዳሳሰበው ገልጾ መንግስት ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ የህግ የበላይነትን እንዲያረጋግጥ አሳስቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መንግሥት በተለያዩ ቦታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ ያላቸውን ጥፋቶች በቅድሚያ መረጃ ሰብስቦ እርምጃ በመውሰድ ሲያከሽፍ መቆየቱን ተናግረው ነገር ግን ያለፈው ሥርዓት ያወረሰንን ቀዳዳዎች ሁሉ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ደፍኖ መጨረስ አልተቻለም ብለዋል።

ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጸጥታ አካላት፣ ምሁራንና ሌሎችም መንግሥት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ የሚወስደውን ርምጃ በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በዳንኤል መላኩ
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *