የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድን ለማስተዳደር ድርድር መጀመሩን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደቡብ አፍሪካን አየር መንገድ ለማስተዳደር እና ወደ ትርፋማነት ለመለወጥ እየተደራደረ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የአየር መንገዱ አለም አቀፍ በረራ አገልግሎት ዳሬክተር አቶ ለማ ያደቻ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት ከደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ ጋር ለረጅም ጊዜ የዘለቁ የንግድ ድርድሮች ከመኖራቸውም ባሻገር አየር መንገዱ ወደመዘጋቱ ደረጃ ከመድረሱ በፊትም በተለያዩ የንግድ ስምምነቶችን ለማድረግ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

አሁንም ያንን የድርድር ሂደት በማስቀጠል የደቡብ አፍሪካን አየር መንገድ ለማስተዳደር እና ወደ ትርፋማነት ለመለወጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርድር መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቅሙም ፤ ክህሎቱም አለው የሚሉት የበረራ ዳይሬክተሩ የደቡብ አፍሪካን አየር መንገድ ለማስተዳደር እና ወደ ትርፋማነት ለመለወጥ ሙሉ እምነትና ዝግጁነቱ አለ ብለዋል፡፡

በዚህም ከደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ ጋር አንዳንድ ውይይቶች የተጀመሩ ሲሆን ወደ ፊት ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተስማማባቸውን ጉዳዮች ጊዜው ሲደርስ ግልፅ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

በዋናነት አየር መንገዳችን በደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ ውስጥ ሊኖረው የሚገባውን ድርሻ በተመለከተ የመጀመሪያ ዙር ጥናቶችን እየተካሄዱ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ በኩል ሁለት አማራጮች እንዳሉ የገለፁት አቶ ለማ የመጀመሪያው በማስተዳደር ወደ ነበረበት ቁመና መመለስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የተወሰኑ የገንዘብ ድጋፎችን በማግኘት አየር መንገዱን ማንቀሳቀስ የሚል መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በዚህ የድርድር ሂደት ውስጥ የተለያዩ የቢዝነስ ሞዴሎች ሊቀርቡ ይችላሉ የሚሉት ዳይሬክተሩ ዋነኛ አላማው ግን የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ የአቪዬሽን ኢንደስትሪውን በጥልቀት ዳግም እዲቀላቀል ማድረግ ነው ይላሉ፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደቡብ አፍሪካን አየር መንገድ ለማስተዳደር እና ወደ ትርፋማነት ለመለወጥ እንቅስቃሴ ጀምሯል ብለዋል፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮችም ሊሳተፉ እንደሚችሉም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህ በፊት ከገበያ የወጡ እና በኪሳራ ላይ የነበሩ የማላዊ፣ዛምቢያ፣ዚምባብዌ እና የቶጎ አየር መንገዶችን ድርሻ በመግዛት ወደ ገበያ እንዲመለሱ ማድረጉ ይታወሳል።

በደረሰ አማረ
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *