የሻሸመኔ ከተማ ፖሊስ በከተማዋ የተለያዩ የሽብር ስራዎችን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ደርሼባቸዋለሁ ያላቸውን አራት ተጠርጣሪዎች መያዙን አስታወቀ።

ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት ሀይማኖተኛ በመምሰል፣የአዕመሮ ህመምተኛ በመምሰል፣የልመና ስራ የሚሰሩ እና ሌሎች ህብረተሰቡ በማይጠረጥራቸው መንገድ ሲንቀሳቀሱ መሆኑን የከተማዋ ጸጥታ ጽህፈት ቤት ገልጿል።

የሀይማኖት አልባሳትን በመልበስ በከተማዋ አከባቢዎች ሲንቀሳቀስ የነበረ ግለሰብ ተይዞ ምርመራ እንደተጀመረበት ተገልጿል፡፡

የከተማዋ አስተዳደር እና የፀጥታ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ስንታየሁ ጥላሁን ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት ከተማዋን ለዳግም ብጥብጥ ሊዳርጉ የሚችሉ እቅስቃሲዎችን በጥንቃቄ ክትትል እየተደረገባቸው እንዳለ ተናግረዋል፡፡

አቶ ስንታየሁ እንደሚሉት ትላንት ማምሻውን እንኳን አራት ስልኮችን የያዘና በአንድ አልቤርጎ ውስጥ ለስድስት ቀናት በመቀመጥ በከተማዋ የተለያዩ ስፍራዎች ያለ ስራ ሲንቀሳቀስ የነበረ አንድ ግለሰብ በክትትል መያዙን ይናገራሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም እብድ በመምሰል ስለላ ሲሰራ የነበርና የተለያዩ ቋንቋዎችን ጠንቅቆ የሚናገር ሌላ ግለሰብም ተይዟል፡፡

የሀይማኖቱ ተከታይ ሳይሆንም የሀይማኖት ልብስ በመልበስ በተመሳሳይ ስለላ እንቅስቃሴ ላይ የነበር እንዲሁ በጸጥታ አካላት መያዙን ነግረውናል፡፡

ከተማዋ አሁን በህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፉ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ሰላማዊ መሆኗን አንስተው ይህንን ለማስቀጠልም የፖሊስ አይንና ጆሮ የሆነው ህብረተሰብ ጥቆማዎችን የማደርሱን ሰራ እንዲያጠናክር አሳስበዋል፡፡

በያይኔአበባ ሻምበል
ሕዳር 2 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *