ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ቀረጥና ታክስ በማጭበርበር የምግብ ዘይትና ጫማ ከውጪ ሊያስገቡ የሞከሩ ነጋዴዎች ተያዙ።

በንግድ ማጨበርበር ሊታጣ የነበረ ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ቀረጥና ታክስ ሊሰበሰብ መሆኑንም የገቢዎች ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቀው በአዳማ እና ሞጆ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በድምሩ ከውጭ የገቡ የምግብ ዘይትና ጫማ መከፈል የነበረበት እና በተሳሳተ ዕቃ መግለጫ መንግስት ሊያጣው የነበረ 16 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ቀረጥና ታክስ ተደርሶበት እንዲሰበሰብ መወሰኑን ገልጧል፡፡

በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ከቀረጥ ነፃ ወደ ሀገር እንዲገባ የተፈቀዱ የምግብ ፍጆታዎች ቢኖሩም ፤ በአዳማ ጉምሩክ ቅ/ጽ/ቤት ከተፈቀደላቸው ታሪፍ ቁጥር ውጪ 14 ሚሊዮን ብር 508 ሺህ 328 ብር ከ 28 ሳንቲም ፤ ቀረጥና ታክስ አጭበርብረው ሊያስገቡ ሲሞክሩ ተደርሶባቸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በሞጆ ጉምሩክ ቅ/ፅ/ቤት በዲክላራሲዮን ቁጥር 4-27474/20 የተመዘገበ ዕቃ አስመጭው ቀረጥና ታክስ ከፍሎ በገቢ ዕቃ አወጣጥ በኩል በዝቅተኛ የስጋት ደረጃ ለእቃው መልቀቂያ ከተሰጠው በኃላ በኢንተለጀንስ በኩል በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ቀደም ሲል ከተገለፀው እቃ ልዩነት ተገኝቷል ብሏል ሚኒስቴሩ::

በዚህ የእቃው አገላለፅ ችግር ምክንያት ሊጭበረበር የነበረ ብር 1 ሚሊዮን 705 ሺህ 473 ብር ከ 30 ሳንቲም እንዲከፈል ተደርጓል ተብሏል ::

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ትኩስ ትኩስ ዜናዎችን፣ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በሔኖክ አስራት
ሕዳር 3 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *