በአዳማ እና በአዲስ አበባ ሁለት የገቢዎች ቢሮ ሰራተኞች ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ ተያዙ።

በአዳማ ገቢዎች ቅ/ጽ/ቤት አንድ ተጠርጣሪ ባለሙያ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ለመቀበል ስምምነት ወስዶ፣ የመጀመሪያውን ዙር ክፍያ ብር 5ዐዐ ሺህ ብር ሲቀበል እጅ ከፍንጅ ሆቴል ውስጥ መያዙን የገቢዎች ሚኒስቴር ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታውቋል፡፡

በምስራቅ አዲስ አበባ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅ/ጽ/ቤት በኦዲት የሥራ ሂደት ውስጥ የቡድን መሪና በዚሁ የሥራ ክፍል ስር አንድ ከፍተኛ ባለሞያ 5 ሚሊዮን ብር ለመቀበል ተስማምተው፤ የመጀመሪያውን ክፍያ ብር 2ዐ0 ሺህ ብር ሲቀበሉ ሁለቱም እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው እንደገለፁት በሁለቱም የገቢዎች ሚኒስቴር ቅ/ጽ/ቤቶች በተሳካው የሕግ ማስከበር ሥራ የግብር ከፋዮቻችን ሚና እጅግ በጣም የሚያኮራ ነበር፡፡

ስለሆነም በዚህ ስኬታማ ሥራ የተሳተፋችሁ አካላትን በሙሉ በራሴና በገቢዎች ሚኒስቴር ሥም ከልብ አመሰግናችኋለሁ ብለዋል፡፡

ሌሎች ግብር ከፋዮችና ሁሉም ኢትዮጵያውያን የራሳችሁና የሀገራችሁ ሀብት በግለሰቦች እንዳይዘረፍና መከፈል ያለበት ግብርም ሳይከፈል እንዳይቀር እንዲሁም የዜግነት ግዴታችሁን በመወጣት እንድትተባበሩና እንድንተጋገዝ ጥሪዬን ለማቅረብ እወዳለሁ ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም የግብርን ፍትሃዊነት እና ህጋዊነት በማረጋገጥ ለጤናማ ኢኮኖሚ ዕድገት ሀገራዊ ሚናችንን ለመወጣት በተግባር እየሰራን እንገኛለን ፤ ወደፊትም አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ትኩስ ትኩስ ዜናዎችን፣ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በሔኖክ አስራት
ሕዳር 4 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *