የተከዜ ሃይል ማመንጫ በቦንም ተመታ ተብሎ የተናፈሰው ወሬ ሀሰት መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ አስታወቀ።

ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ መረጃ ለህዝብ እያደረሰ የሚገኘው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ በማህበራዊ ድረገጹ እንዳስታወቀው ተከዜ ሀይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ ልክ እንደ ሌሎቹ የኃይል ማመንጫ ግድቦች ሁሉ በፌደራል መንግሥት የተገነባና የሚያስተዳድረውም የፌደራል መንግሥት ነው።

እሁድ ጥቅምት 29፣ 2013 ዕለት የህወሓት ሚሊሻ ግድቡን ለመጠበቅ የተሠማራውን የፌደራል ፖሊስ ኃይል ከሥራው ለማደናቀፍ ጥቃት ፈጽሟል።

የተጎዱት እና የተገደሉት ቁጥር ያልተረጋገጠ ቢሆንም፣ በሕይወት የተረፉት 11 የፌደራል ፖሊስ አባላት ለ14 ሰዓት ያህል በእግር ተጉዘው፣ ተራራዎችን አቆራርጠው ወደ ጎንደር ገብተዋል።

በቀጣዮቹ ቀናት የህወሓት አክቲቪስቶች በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት “ግድቡን ተቆጣጥረናል” የሚል መረጃ ማሰራጨታቸው ተስተውሏል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የህወሓት ሚልሻዎች በማይካድራ በንጹሀን ዜጎች ላይ የፈፀሙትን ጭፍጨፋ አስመልክቶ ሪፖርት ባወጣበት በህዳር 3፣ 2013 ዕለት፣ የህዝብን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር የተከዜ ግድብ በቦንብ እንደተመታ የሚያትት ሆን ተብሎ የተቀናበረ፣ የሀሰት መረጃን ህወሓት በቴሌቪዥን አሰራጭቷል ብሏል።

ባለሁለት ክበብ ቅስት ያለው እና በውሀ የተሞላ ግድብ በቦንብ ቢመታ ሊያስከትል የሚችለው መጥለቅለቅ እና ጥፋት ማንም ሊገምተው የሚችለው መሆኑ የመረጃውን ሀሰተኛነት በቀላሉ ማረጋገጥ እንደሚቻል ይሄው ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ መረጃ የሚያቀብለው የመረጃ ተቋም አስታውቋል።

ተፈጥሯዊ ባህሪው ነውና፣ በህወሓት ውስጥ የሚገኘው የጽንፈኞች ቡድን በሀሰት ለማሳመን ጥረት ማድረጉን ይቀጥላል። ህወሓት የሀሰት መረጃ የማሠራጨት ዘመቻውን በትጋት መቀጠሉን ሁሉም ሰው እንዲገነዘብ በድጋሚ ለማሳሰብ እንወዳለንም ብሏል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ትኩስ ትኩስ ዜናዎችን፣ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

ኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮጵያዊያን
ሕዳር 4 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *