በትግራይ ክልል ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ክልሉ በጊዜያዊ አስተዳድሩ መመራቱ እንደሚቀጥል የፌደራል ዲሞክራሴ ግንባታ ማዕከል አስታወቀ።

በትግራይ ክልል እየተወሰደ ያለው ህግን የማስከበር ስራ እንደተጠናቀቀ ክልሉ በጊዜያዊ አስተዳድሩ ከተመራ እና ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ ከተፈጠረ በኋላ ምርጫ እንደሚካሄድም ማዕከሉ ገልጿል።

በክልሉ ህግ የማስከበር ስራው ሲጠናቀቅ ክልሉ ምን ይሆናል? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።

በጉዳዩ ላይ ያናገርናቸው የፌደራል ዲሞክራሴ ግንባታ ማዕከል አስተባበሪ ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት የትግራይ ክልል ህዝብ ለነጻነት ፤ለሰላም እና ራስን በራስ ለማስተዳደር ለእኩልነት በጣም ከፍተኛ ዋጋ የከፈለ ኩሩ ህዝብ ነው ብለው፡፡

ህዝቡን ከህወሃት አምባገነን ቡድን ነጻ የማውጣት እና ህግን የማስከበር ስራው እንደተጠናቀቀ ጊዜያዊ አስተዳድር ይቋቋማል በመቀጠልም በምርጫ የራሱን አስተዳድር እና ክልላዊ መንግስት ያቋቁማል ሲሉ ዶክተር ብቂላ ተናግረዋል።

በህገመንግስቱ መሰረት አንድ ክልልም ሆነ በፌደራል መንግስቱ ውስጥ ስልጣን የሚያያዘው በምርጫ እና በህዝብ ይሁንታ ብቻ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

በትግራይ ክልል አሁን ባለው ህገወጥ አካሄድ ምክንያት ከፍተኛ የሆኑ የህግ ጥሰት በማጋጠሙ ምክንያት በክልሉ ውስጥ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም የፌደሪሽን ምክር ቤት ቀድም ብሉ መወሰኑን አስታውሰዋል።

አሁን ግን ቅድሚያ የህግ ማስከበሩን ሂደት እያከናወንን ከስር ከስር ትግራይ ክልል ውስጥ ጊዜያዊ አስረዳደር ይዋቀራል ብለዋል ዶ/ር ቢቂላ፡፡

ባለፈው ሳምንት የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳድርን በተመለከተ የክልሉ ህዝብ እንዲያውቅ የምንፈልገው ይህ አስተዳድር በስራ ላይ የሚቆየው ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ብቻ መሆኑን ነውም ብለዋል ዶክተር ቢቂላ።

የጊዜያዊ አስተዳድሩ ሃላፊነቶች ህዝቡ መደበኛ አገልግሎቶችን እንዲያገኝ፣እንዲረጋጋ ፣እና ሌሎች መንግስታዊ አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ መስጠት እንደሆነም ዶክተር ቢቂላ ገልጸዋል።

የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴዕታ የነበሩት ዶክተር ሙሉ ነጋ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳድር ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው መሾማቸው ይታወሳል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ትኩስ ዜናዎችን፣ ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በያይኔአበባ ሻምበል
ሕዳር 7 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.