የእሳት እና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቅው ባሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ አራት የእሳት አደጋዎች መከሰታቸውን አስታውቋል፡፡
የመጀመርያው የእሳት አደጋ የተከሰተው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ በአንድ መኖርያ ቤት ላይ የደረሰ የእሳት አደጋ ነው፡፡
በዚህ አደጋ 100 ሺህ ብር የሚጠጋ ንብረት አደጋ የደረሰበት ሲሆን ከሁለት ሚሊየን ብር በላይ የሚሆን ንብረት ደግሞ ማዳን እንደተቻለ ነው የተገለጸው፡፡
ሁለተኛ አደጋ የደረሰው ደግሞ በኮልፌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት በመኖርያ ቤት የደረሰ የእሳት አደጋ ነው፡፡
በዚህኛውም አደጋ ምክንያት ከአምስት ሺህ ብር በላይ በሚሆን ንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ከሶስት ሚሊየን ብር በላይ የሚሆን ንብረት ደግሞ ማዳኑን ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው፡፡
ሌላኛው የእሳት አደጋ የደረሰው በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት በአንድ መኖርያ ቤት ላይ የደረሰ አደጋ ነው፡፡
ከዚህኛው አደጋ ጋር በተያያዘም 50 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ንብረት ከውድመት ማዳኑን ነው የገለጸው፡፡
አራተኛ አደጋ የደረሰው ደግሞ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሶስት የኮንስትራክሽን እቃዎች በተከማቹበት መጋዘን ውስጥ የተከሰተ ድንገተኛ የእሳት አደጋ ነው፡፡
ከአደጋው 80 ሺህ ብር የሚሆን ንብረት የወደመ ሲሆን ከ800 ሺህ ብር በላይ የሚጠጋ ንብረት ደግሞ ማዳን እንደተቻለ ነው የእሳት እና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግኑኝነት ሀላፊ አቶ ጉልላት ጌታነህ የነገሩን፡፡
በሔኖክ ወ/ገብርኤል
ሕዳር 7 ቀን 2013 ዓ.ም











