በትናንትናው ዕለት በሻሸመኔ ከተማ ችግር ለመፍጠር የሞከሩ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን የከተማዋ ጸጥታ ጽህፈት ቤት ገልጿል።
ትላንት በሻሸመኔ ከተማ መውጫ በሮችና አንዳንድ ስፍራዎች ይንቀሳቀሱ በነበሩ መኪኖች ላይ ድንጋይ በመወርወርና መንገድ በመዝጋት ጥቃት ለመፈጸም ከሞከሩት ውስጥ 16 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የከተማዋ አስተዳደር እና የፀጥታ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ስንታየሁ ጥላሁን ለኤትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
አቶ ስንታየሁ እንዳሉት ዕድሜያቸው ከ15 አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎቸን ለዚህ አይነት ተግባር ማሰማራት በእጅጉ ሞራለ ቢስነት ነው፡፡
ሃላፊው አክለውም እንዳለፈው አይነት ውድመት በከተማዋ አደርሳለሁ ብሉ ማሰብም አደገኛ ነው ብለዋል፡፡
የከተማዋ አስተዳደር እንዲህ አይነት ተግባሮችን ፈጽሞ አይታገስም ያሉት አቶ ስንታየሁ እኚህ ታዳጊዎች ማን እና ለምን እንዳሰማራቸው ፖሊስ ምርመራ ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ታዳጊዎች በከተማዋ ውስጥ ብጥብጥ በማስነሳት የመንግስትን ትኩረት የመበተን አቅጣጫ እንደተሰጣቸው መናገራቸውን ይናገራሉ አቶ ስንታየሁ፡፡
በከተማዋ እና አጎራባች አከባቢዎች የተፈጠሩ ችግሮችን በአስቸኳይ እንዲቆጣጠሩና ዳግም እንዲህ አይነት ሙከራ እንዳይደረግ ከወዲሁ ጠንካራ ክትትል እንዲያደርጉ ትዕዛዝ መተላለፉንም ሃላፊው አብራርተዋል፡፡
በያይኔአበባ ሻምበል
ሕዳር 14 ቀን 2013 ዓ.ም











