ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሹም ሽር እያካሄደ ነው።

በቅርብ ቀናት ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነታቸው ተነስተው ወደ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት የተዛወሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ በተቋሙ ውስጥ የሚታዩ የተጋላጭነት ቀዳዳዎችን ለመድፈን ይረዳል የተባለ ሰፊ የሹምሽር እያደረጉ ነው።

አዲሱ ሹም ሽር የተደረገው አሁን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ሆነው የተሾሙት ደመላሽ ገብረ ሚካኤል መስሪያ ቤቱን ከመልቀቃቸው በፊትና ከለቀቁ በሁዋላ የተደረገ የስጋት ግምገማን መነሻ በማድረግ እንደሆነም መረዳት ችለናል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ የደህንነት መስሪያ ቤትን አሰራር ለማሻሻልና በኢህአዴግ አስተዳደር ዘመን የነበረውን ቅጥ ያጣ ስልጣን በህግ ለመገደብ የሚያስችሉ ስራዎች ቢከናወኑም በተመሳሳይ ግን ተቋሙ መሰረታዊ በሆኑ የሀገሪቱ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ በነበረው አፈጻጸም ደካማ ነበር የሚል ትችት ቀርቦበታል።

በኦሮምያና ሌሎች ክልሎች የበርካቶችን ህይወት የቀጠፉ የጸጥታ ችግሮች ሲፈጠሩ ፣ በትግራይ ክልል መጠነ ሰፊ የጦርነት ዝግጅቶች ሲደረግ ፣ በኦነግ ሸኔም ሰፊ ጥፋቶች ሲደርሱ አስቀድሞ ለመከላከል የሚረዱ የደህንነት ስራዎችን በተገቢው ፍጥነትና ጥራት ማከናወን ላይ ጉድለቶች ታይተውበታል ተብሏል።

መስሪያ ቤቱ ” የጸረ ለውጥ ” ቡድን አባላት ተባባሪ የሆኑ ጥቂት ሰራተኞች እንደነበሩበት በማመንም እርምጃዎችን ወስዷል።በተቋሙ በቁልፍ ሀላፊነት ላይ ያሉ አመራሮች ሹምሽር የተደረገው ጉድለት ተብለው ከቀረቡት የግምገማ ግኝቶች በመነሳት ነው።በዚህም መሰረት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አሰፋ አብዩ ከሀላፊነታቸው መነሳታቸውን ሰምተናል። አሰፋ አብዩ ወደ ደህንነት መስሪያ ቤት ከመምጣታቸው በፊት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ነበሩ።

በቅርቡ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራልነታቸው የተነሱት እንደሻው ጣሰው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል።እንዲሁም የፀረ ስለላና የፀረ ሽብር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማህበራት ክትትል መምሪያ ኃላፊ ፣ የሀገር ውስጥ ደህንነት ፀረ ስለላና የአየር መንገድ እና ኢምግሬሽን ደህንነት ኃላፊ ፣ የአስተዳደርና ኦፕሬሽን ዘርፍ ሀላፊን ጨምሮ ሌሎች ስድስት አንጋፋ ባለሙያዎችና የዘርፍ አመራሮች ከሀላፊነት እንዲነሱ ተደረጓል።

የሹም ሽሩ በዚህ እንደማያበቃና ተቋሙ አዳዲስ ለውጦችን በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል ሲል ዋዜማ ራዲዮ ዘግቧል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ።
https://t.me/ethiofm107dot8

ኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮጵዮዊያን
ሕዳር 15 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *