በኢትዮጵያ ከ7 ሺህ 500 በላይ ሕጻናት የልብ ቀዶ ጥገና ህክምና ለማድረግ ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ናቸው ተባለ።

በኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ የህዝብ ግንኙነት ተጠሪ አቶ ናሆም ስንታየሁ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት ከ7 ሺህ 500 በላይ ህጻናት የልብ ቀዶ ጥገና ህክምና ለማድረግ ወረፋ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ነግረውናል።

በሙሉ አቅማችን ስንሰራ በሳምንት ከ5 እስከ 7 ህጻናትን ልናክም እንችላለን ያሉት የህዝብ ግንኙነት ተጠሪው በአሁኑ ወቅት ግን የአላቂ እቃዎች እጥረት ስላለብን በሳምንት ከ 2 እስከ 3 ህጻናትን ብቻ ነው እያከምን ያለነው ብለዋል።

ማዕከሉ በተደጋጋሚ እንደሚገልፀው ያለምንም የባለሙያ ችግር በሙሉ አቅሙ እየሰራ ይገኛል ተብሏል።

ነገር ግን የሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታና የኮሮና ቫይረስ በሀገር ውስጥ የምናገኝ የነበረውን ገቢ ቀንሶብናል ያሉት አቶ ናሆም ከውጭ ሀገር መጥተው የህክምና ድጋፍ የሚያደርጉልን በጎ ፍቃደኞችም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት መምጣት አልቻሉም ሲሉ አክለዋል።

የሀኪሞችን ደሞዝ በተመለከተም የጤና ሚኒስቴር ለሁለት አመት እከፍላለሁ ብሎ ቃል በገባው መሰረት ክፍያው እንደቀጠለም ለማወቅ ችለናል።

ማዕከሉ የልብ ተከፍቶ ህክምና እና ልብ ሳይከፈት የሚደረግ ህክምናን እየሰጠም ይገኛል።

በዶክተር በላይ አበጋዝ መስራችነት የተቋቋመው በኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ 31 አመት ያስቆጠረ ሲሆን የልብ ማዕከሉ ደግሞ የ12 አመት እድሜ አለው።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በመቅደላዊት ደረጀ
ሕዳር 17 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *