በጦርነት ቀጠና ውስጥ ያለው የመተማና ሑመራ አካባቢዎች የሰሊጥ ምርት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መሰብሰቡ ተገለጸ።

ከፍትኛ የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ የግብርና ምርቶች ውስጥ ሰሊጥ አንዱ ሲሆን በተለይም በእስያ እና አውሮፓ አገራት ፋብሪካዎች ተፈላጊ ነው።

በሰሜን ኢትዮጵያ በተጀመረው የህግ ማስከበር ዘመቻ ምክንያት ሰብሉ ሳይሰበሰብ ለብክነት ይዳረጋል የሚል ሰፊ ስጋትም ነበር።

ይሁንና በመተማና ሁመራ አካባቢ ያለው የሰሊጥ ምርት ከ92 በመቶ በላይ መሰብሰቡን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በሚኒስቴሩ የሰብል ልማት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ኢሳያስ ለማ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት በዓመቱ የሰሊጥ ምርት ተሰብስቧል፡፡

በመላ አገሪቱም ከ13 ሚለየን ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥ የተሸፈነ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው የሰሊጥ ምርት የሚገኘው በሁመራ እና መተማ አካባቢዎች ነው።

በኦሮሚያ፣ደቡብ እና ጋምቤላ ክልል ያለው የሰሊጥ ምርትም ከ70 በመቶ በላይ መሰብሰቡ ተገልጿል፡፡

በተያያዘ ዜናም ቀድመው የሚደርሱት የአብዛኛው የቆላማ አካባቢዎችም ስንዴን ጨምሮ በቆሎና ጤፍ እየተሰበሰበ ይገኛል ያሉን ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ማሽላ እየደረሰ ይገኛል ብለውናል፡፡

በቀጣይ በአብዛኛው ሰብል የሚሰበሰበው ከህዳር አጋማሽ ጀምሮ እስከ ታህሳስ መጨረሻ ድረስ መሆኑን ያነሱልን አቶ ኢሳያስ በዚህ ጊዜ ውስጥ በደጋማው የሃገሪቱ ክፍል ላይ የሰብል መሰብሰቡ ሂደቱ እንደሚቀጥል ነግረውናል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በየውልሰው ገዝሙ
ሕዳር 17 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *