በአዲስ አበባ ከ107 ሺህ በላይ ሰዎች ኤች አይ ቪ ኤድስ በደማቸው እንዳለ ተገለፀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠሪያ ፅ/ቤት በነገው እለት ቦሌ ለሚ ኢንደስትሪያል ፓርክ የሚከበረውን የአለም የኤድስ ቀን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።

በአለም አቀፍ እና በሀገራችን በየአመቱ ህዳር 22 ቀን የሚከበረው የአለም የኤድስ ቀን ዘንድሮም የኤች አይ ቪን ለመግታት ፤ አለም አቀፋዊ ትብብር ፤ የጋራ ሀላፊነት በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ተገልጷል።

በፅ/ቤቱ የዘርፍ ብዙ ምላሽ ዳሬክተር ሲ/ር ፈለቀች አንዳርጌ በመግለጫቸው እንዳሉት በመዲናዋ ኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት አሁንም ትኩረትን ይሻል።

በአዲስ አበባ በየአመቱ 18 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ህይወታቸውን ያጣሉ ብለዋል።

በአዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት ከ107 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች ኤች አይ ቪ ኤድስ በደማቸው እንዳለ የገለፁት ሲ/ር ፈለቀች ከዚህ ቁጥር ውስጥ ተመርምረው እራሳቸውን ያወቁት 79 በመቶዎቹ ብቻ በመሆናቸው ራሳቸውን ያላወቁት ሰዎች አሁንም ቫይረሱን እያስተላለፉ አልያም በቫይረሱ ራሳቸውን እየጎዱ ነው ብለዋል።

ፅ/ቤቱ 90 በመቶ የሚሆኑት የማህበረሰብ ክፍሎች ለመለየት እቅድ ቢይዝም ማሳካት የተቻለው 79 በመቶ ብቻ ሲሆን ይኸውም ዝቅተኛ አፈፃፀም ነው ሲሉ ገልፀዋል።

ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች ወደ ጤና ተቋማት ሄዶ የመመርመር ተነሳሽነት ዝቅተኛ መሆን ባቀድነው ልክ መራመድ አለመቻሉን አንስተዋል።

አጠቃላይ የስርጭት መጠኑ 3 ነጥብ 2 በመቶ መድረሱንም ዳይሬክተሯ ገልፀዋል።

በጠቅላላ በሀገር ደረጃ ያለው የቫይረሱ ስርጭት እንዲሁ ከፍተኛ መሆኑ ተጠቁሟል።

በኢትዮጵያ በየአመቱ ከ 18 እስከ 20 ሺህ የሚገመቱ ወገኖች አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ መሆናቸውን የሚናገሩት ሲ/ር ፈለቀች በተመሳሳይ ከ18 ሺህ በላይ ዜጎች ህይወታቸውን እንደሚያጡ ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ 669 ሺህ በላይ ዜጎች በኢትዮጵያ ኤች አይ ቪ ኤድስ በደማቸው እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።

በሀገራችን የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን እና ተፅዕኖ ለመከላከል እንዲሁም ለመቆጣጠር መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ፤ የሲቪክ ማህበራት እና በማህበረሰቡ የተቀናጀ ስራ የተመዘገቡ ውጤቶች ቢኖሩም አሁንም ግን የኤድስን ስርጭት መግታት የጋራ እርብርብ ይጠይቃል ተብሏል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በደረሰ አማረ
ሕዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.