የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች እና ረዳት አሽከርካሪዎች የኮቪድ-19 የህይወት ኢንሹራንስ ተገባላቸው::

የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች በኮቪድ-19 ህመም ምክንያት ከስራ የሚርቁ ከሆነ ለሁለት ተከታታይ ወራት በየወሩ ስድስት ሺህ ብር የሚከፈላቸው ሲሆን፤ ረዳት አሽከርካሪዎች ደግሞ ለሁለት ተከታታይ ወራት በየወሩ ሶስት ሺህ ብር ይከፈላቸዋል ተብሏል።

መድህን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ፣ የመድህን ሰጪዎች ማህበርና የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን በጋራ በሰጡት መግለጫ የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎችና ረዳት አሽከርካሪዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ለሚያጋጥማቸው ህመምና የሞት አደጋ መድህን ተገብቶላቸዋል ብለዋል።

በኮቪድ-19 የሞት አደጋ ያጋጠማቸው የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ለቤተሰቦቻቸው 250 ሺህ ብር የመድህን ካሳ የሚከፈል ሲሆን በኮቪድ-19 የሞት አደጋ ያጋጠማቸው የድንበር ተሻጋሪ ረዳት አሽከርካሪዎች ደግሞ ለቤተሰቦቻቸው 150 ሺህ ብር የመድህን ካሳ እንደሚከፈል ተገልጿል።

የመድህን ክፍያው ወጪ የሚሸፈነው በመድህን ሰጪ ተቋማትና በኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን በኩል እንደሆነ ታውቋል።የመድህን ሽፋኑን ለመስጠት በብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የተሰጣቸው ስምንት የመድህን ሰጪ ተቋማት ተሳታፊ ይሆናሉ።

ኢንሹራንሱ ለአንድ አመት የሚያገለግል ሲሆን አመቱ እንዳበቃ ዕድሳት ይደረጋል ተብሏል፡፡ የኢንሹራንስ ሰርተፍኬቱን ያልያዘም አሽከርካሪም ድንበር መሻገር እንደማይችል ተገልጧል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
ድረ ገጻችንን https://ethiofm107.com/ ይጎብኙ::

ሔኖክ አሥራት
ታህሳስ 16 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.