ሱዳን የድንበር ላይ ትንኮሳዋን የማታቆም ከሆነ አፀፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ ኢትዮጵያ አስጠነቀቀች።

የዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀዉ ሱዳን በድንበር አካባቢ እያደረሰች ያለዉን ህገወጥ ድርጊት የማታቆም ከሆነ ኢትዮጵያ ሉኣላዊነቷን ለመጠበቅ ስትል እርምጃ ትወስዳለች ብሏል፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት የሱዳን ኃይል የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ በመግባት በርካታ ህገወጥ ድርጊቶችን ፈፅሟል።

ይህም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል እያደረገ ያለዉን የህግ ማስከበር ተልዕኮ እንደ ክፍተት ተጠቅመዉ ኢትዮጵያን እና ሱዳንን ወደ ግጭት እንዲያመሩ ከከሚፈልጉ ሃይሎች የመነጨ ነዉ ብለዋል፡፡

“ኢትዮጵያ ሉኣላዊነቷን ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆኗን ያረጋገጡት ቃል አቀባዩ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ እንፈታለን ስንል ፍርሃት ከመሰላቸዉ ተሳስተዋል፤ ማንኛዉንም ጥቃት ለመመከት የፀጥታ ሃይሉ 24 ሰዓት በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል” ብለዋል፡፡

ቃል አቀባዩ የኢትዮጵያን ዉድቀት የሚመኙ አገራት መኖራቸዉን የተናገሩ ሲሆን ኢትዮጵያ በነጻነቷ ከመጡባት ማንንም እንደማትምር ከታሪካችን መረዳት ይኖርባቸዋልም ብለዋል።

የሱዳን ህዝብ እና መንግስት ከሚጎትታቸዉ ሃይል እራሳቸውን እንዲቆጥቡም አምባሳደር ዲና አሳስበዋል፡፡

ሱዳን እና ኢትዮጵያ በበርካታ ዘርፎች ላይ ታሪካዊና መልካም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸዉ በተደጋጋሚ ሲነገር ይደመጣል፡፡

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ሱዳን በህዳሴዉ ግድብ ላይ ያላትን አቋም መለዋወጥ ጀመረች ሰነብታለች።

አሁን ደግሞ የአገሪቱ ጦር የኢትዮጵያን ድንበር በመጣስ በምእራብ ጎንደር አካባቢ በርካታ ጥፋቶችን እያደረሰ እንደሚገኝ በአካባቢው ነዋሪዎች እና አስተዳድር ተገልጿል፡፡

የሱዳን ጦር እያደረገ ያለው ድርጊት ሙሉ በሙሉ የሱደን መንግስት አቋም ባይሆንም የሱዳንን ህዝብ ለዘመናት ሲገዙት የነበሩ አገራት ዛሬም ያንን ለመድገም በመፈለጋቸው መሆኑን አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።

በአባቱ መረቀ
ታህሳስ 20 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.