የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በዳርፉር ሰፍረው የሚገኙትን ወታደሮች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ያስተላለፈውን ውሳኔ በመቃወም በተቀሰቀሰው ግጭት እስካሁን ድረስ 18 ያህል ሰዎች መሞታቸውን ነው የተነገረው፡፡
በዳርፉር የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሀይል እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወታደሮች ሰፍረው ይገኛሉ፡፡ የሁለቱ ድርጅት ወታደሮች ወደ አካባቢው የገቡት በሱዳን በሁለት ጎሳዎች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ለማረጋጋት ነበር፡፡
የዳርፉር ግዛት አስተዳዳሪ ባስተላለፉት መልእክት የእርቁ ጊዜ በመጠናቀቁ ሁሉም ነገር መልክ ሊይዝ የግድ ይላል ብለዋል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው አክለው እንደተናገሩትም ከዚህ በኃላ በእርቅ ሰበብ የሰው ሂወት እንዲጠፋ የሱዳን መንግስት አይፈልግም ብለዋል፡፡
ባካባቢው ግጭቱ በማገርሸቱም የሀገሪቱ ባለስልጣናት ወደ አካባቢው ተጨማሪ ወታደሮች እንዲሰማሩ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ነው የተሰማው፡፡
ሱዳን ትሪቢውን እንደዘገበው ግጭቱ የተከሰተበት አካባቢ በተደጋጋሚ ግጭት የሚከሰትበት ቀጠና ነው ብሏል፡፡
አሁን ላይ በግጭቱ የተሳተፉ አካላትን የማደኑ ስራ መቀጠሉን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
በሔኖክ ወ/ገብርኤል
ታህሳስ 20 ቀን 2013 ዓ.ም











