በምርጫ ቦርድ የተሰረዘው ኢዴፓ ለነገ የጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተንዛዛ አሰራር ምክንያት መሰረዙን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ኢዴፓ እንዳስታወቀው ለነገ ታህሳስ 23 ቀን 2013 ዓ.ም በሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት የያዝነው ፕሮግራም ተሰርዟል ብሏል።

ፓርቲው ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቀው በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የተላለፈብንን የስረዛ ውሳኔ አስመልክቶ ለነገ ጋዜጣዊ መግለጫ ጠርቶ ነበር።መግለጫ ሊሰጡበት በታሰበው ሆቴሉ አካባቢው ያለው የካራማራ ፓሊስ ጣቢያ ፈቃድ አምጡ አለን እዛ ሄድን እነሱ ደግሞ ለቦሌ ክ/ከተማ ፓሊስ መምሪያ ላኩን እነሱ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ልከውን ነበር።

ኮሚሽነሩን አናገርናቸው።እሳቸው ደግሞ ከንቲባ ፅ/ቤት ሄዳችሁ የሰላማዊና ህዝባዊ ስብሰባ ፈቃድ ክፍል ፈቃድ አምጡ አሉን ብሏል ፓርቲው።እኛም ሰልፍም አይደለም፣ ስብሰባም አይደለም ጋዜጣዊ መግለጫ ነው የምንሰጠው።ከዚህ በፊትም ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ስንፈልግ ይሄን ተጠይቀን አናውቅም።

አሁን ምን የተለየ ነገር ተገኝቶ ነው አልናቸው። እሳቸውም ብዙ ነገር ተለውጧል። አዳዲስ ፕሮቶኮሎችም ወጥተዋል ብለው ለነገ እንደማንችል አሳውቀውናል ብሏል። እስካሁንም ያለውን ሂደት የተጓዝነው እየጠየቁን ያለው ተገቢ ጥያቄ ሆኖ ሳይሆን ማስጨረስ ስለነበረብን ነው።

በመጨረሻ ያረጋገጥነው ግን ምን ያህል ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት አደጋ ውስጥ መውደቁን ነው ብሏል ፓርቲው። ባለው የተጣበበ ሰዓት እና ሁኔታ ምንም ማድረግ ስለማንችል መግለጫው የተሰረዘ መሆኑን ከይቅርታ ጋር እንገልጻለን ብሏል ፓርቲው።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ በበኩላቸው ፓርቲው በኮሚሽኑ ላይ ባቀረበው አቤቱታ ዙሪያ ላቀረብንላቸው ጥያቄ በፓርቲው ስለቀረበው አቤቱታ መረጃው የለኝም ብለውናል።

ኢዴፓ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አደረኩት ባለው የአባላት ማጣራት ዝቅተኛውን መስፈርት አላሟላም በሚል መሰረዙ ይታወቃል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
ድረ ገጻችንን https://ethiofm107.com/ ይጎብኙ::

በሳሙኤል አባተ
ታህሳስ 22 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *