የፖለቲካ ታሪክ መግነን ብሔራዊ ስሜትን አሳጥቷል ተባለ፡፡

በኢትዮጲያ ታሪክ በመንግስት ለውጥ ሂደት ውስጥ የነበረው የርዕዮተ ዓለም መለዋወጥ እና ሌሎች ተያያዥ ክስተቶች የጋራ ታሪክን ማሳጣቱ ተነግሯል፡፡

በዛሬው እለት የሰላም ሚኒስቴር ባዘጋጀው “የታሪክ ሚና በብሔራዊ መግባባትና በሀገር ግንባታ” በሚል እርዕስ የውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡

በዚህም በተለየ መልኩ የፖለቲካ ታሪክ መግነኑ ብሔራዊ ስሜትን አሳጥቷል ሲሉ የመወያያ ፅሁፍን ያቀረቡትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአለ የስነ ጥበብ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ተናግረዋል።
ከእዚህ በተጨማሪ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ወይም ከ1 እስከ 8 ያለው ስርዓተ ትምህርት በክልሎች እንዲዘጋጅ መደረጉ የተዛቡ የሀሰት ትርክቶች እንዲበዙ እና የጋራ መግባባት እንዳይፈጠር ምክንያት ሆኗል ሲሉ ረ/ፕ አበባው አንስተዋል።

ከዛም ባሻገር ታሪክ ማለት ጥሩ ጥሩዎቹ ብቻ ተመርጠው ሲተረኩ አይደለም ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ለምሳሌ” ከሰሞኑ በመንግስት ህግ ማስከበር ሂደት ጋር የተፈጠረውም ታሪክ መሆን አለበት” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እየተመረጠ እና እየተስተካከለ የሚቀመጥ ታሪክ መኖር የለበትም ብለዋል ረዳት ፕሮፌሰር አበባዉ፡፡

ታሪክን በአግባቡ ለማስቀመጥና ለተተኪዉ ትዉልድ ትክክለኛዉን ታሪክ ለማስተላለፍም ታሪክን ለታሪክ ምሁራን መተው ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በረድኤት ገበየሁ

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *