በትግራይ ክልል ብዙሃን መገናኛ በህወሀት ቡድን ተገደው ሲሰሩ ለነበሩ ጋዜጠኞች ስልጠና ሊሰጥ እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አስታወቀ።

በትግራይ ክልል በነበረው ህግ የማስከበር ዘመቻ፣ ከአገልግሎት ተቋርጠው ከነበሩ ተቋማት መካከል የመገናኛ ብዙሃን ይገኙበታል።

ህግ የማሰከበር ዘመቻው ማብቃቱን ተከትሎ ደግሞ የመገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ መደበኛ ስራቸው በመመለስ ላይ ናቸው።

በአሁኑ ሰኣት በክልሉ ያለውን የመገናኛ ብዙሃን እንቅስቃሴ አስመልክቶ የባለሥልጣኑ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊው አቶ አበራ ወንድወሰን ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት፣ የትግራይ ክልል ፋና ኤም፣ ኢቢሲ፣ ኦቢኤን እና የአማራ ማስ ሚዲያ መደበኛ ስራቸውን እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

አቶ አበራ በክልሉ እነዚህ የመገናኛ ብዙሃን አይነቶች ለማህበረሰቡ የመረጃ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን፣ ምንም እንኳን የትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ስርጭት ቢጀምርም ስርጭቱ ግን የተጠናከረ አይደለም ነው ያሉት።

ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ከህወሀት ቡድን ጋር አብረውና በዚህ ሃይል ተገደው ሲሰሩ የነበሩ ጋዜጠኞች የነበሩበት በመሆኑ ነው ብለዋል።

ስለሆነም በቴሌቭዥኑ ላይ ሊሰሩ የሚችሉ በቂ የሆነ የሰው ሃይል ባለመኖሩ መደበኛና የተጠናከረ ስርጭቱን እንዳይጀምር ሆኗል ብለዋል።

ብሮድካስት ባለስልጣኑ በክልሉ ቴሌቪዥን ተገደውና ሳይገደዱ ሲሰሩ የነበሩትን ጋዜጠኞች የመለየት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝና ተገደው ሲስሩ እንደነበር በልየታ ከታወቀ በኋላ በቅርቡ ስልጠና እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል።

ጋዜጠኞችን አስልጥኖ ለመመለስና የክልሉ ማህበረሰብ ሙሉ በሙሉ የመረጃ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነም ሃላፊው ተናግረዋል።

በጅብሪል ሙሀመድ
ጥር 3 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *