ኦፌኮ ከሀገራዊ ምርጫው ተገድዶ ሊወጣ የሚችልበት ዕድል መኖሩን ተናገረ::

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ፖርቲ በሀገራዊ ምርጫው ስለመሳተፉ እስካሁን እንዳልወሰነ ተናግሯል፡፡የፖርቲው ተቀዳሚ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ለኤትዮ ኤፍኤም እንዳሳወቁት በመላ ኦሮሚያ በሺዎች የሚቆጠሩ አባሎቻችን ታስረዋል፤በመቶዎች የሚቁጠሩ ቢሮዎቻችን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተዘግተዋል ፤በሰላም የመንቀሳቀሱ ጉዳይም ችግር በመኖሩ ከምርጫው ገፍተን ልንወጣ እንችላለን ብለዋል፡፡

ህዝቡ አትግቡ ካለ መግባት ይቸግራል የሚሉት ፕሮፌሰር መራራ በተለያየ አጋጣሚ ደጋፊዎቻችን ሰውን እያሳሰራችሁ የት ልትገቡ ነው የሚል ምላሽ እየሰጡን በመሆኑ የበለጠ ችግር እንዳይከሰትም በምርጫው ላለመሳተፍ እያጤንን ነው ይላሉ፡፡

እኛ አሁን እያሳሰበን ያለው ነገር በምርጫ መሳተፍና አለመሳተፍ ሳይሆን ቀጣዩ የሀገሪቱ አንድነት ነው፡፡ሁሉም ዜጋ በጋራ የሚኖሩባት የሚግባቡባት እንድትሆን ከአዳራሽ ያለፈ ብሔራዊ መግባባት የሚያመጡ መድረኮች ያሰፈልጋሉ ፤ ቅድሚያ እዚያ ላይ መደረስ አለበት ነው የሚል አቋም ፖርቲያችን አለው ነው የሚሉት፡፡

ባለፉት ሀምሳ አመታት የሚጋጩ ህልሞችን ይዘን ተጉዘናል የሚሉት ፕሮፌሰር መራራ አንድ ቦታ በቃን ብለን የሁላችንም ህልም የሚስተናገድበትን ወይም የሚቀራረብበትን ሙሉ ለሙሉ እንኳን ማስታረቅ ባንችል በሰለጠነ ፖለቲካ የምንይዝበትን መንገድ ካልፈጠርን በስተቀር ከሳሽና ተከሳሸነቱ አብሮን ይኖራል ባይ ናቸው ፡፡

ለዚህ ደግሞ ሁሉም ጣቱን ሌላው ላይ ከመቀሰሩ በፊት ራሱን ማየት ይኖርበታል ነው የሚሉት፡፡ህዝቡ አሁን የሚፈልገው ሰላም ነው ለዚህ ደግሞ ፖለቲከኞችም ይሆኑ ሊሂቃኑ ራሳቸውን ከእኔ ይበልጣል ትርክት ማላቀቅ አለባቸው ብለዋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ::

ያይኔ አበባ ሻምበል
ጥር 4 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *