ኢትዮጵያ በመጭው ክረምት በአጎራባች አገራት ድንበሮች አካባቢ 1 ቢሊዮን ችግኝ ልትተክል መሆኑን አስታወቀች።

ለመጭው ክረምት የሚተከለውን ችግኝ ለማፍላት 100 ሚሊዮን ብር መመደቡም ተገልጿል።

ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልዩ ትኩረት የሰጠችው ኢትዮጵያ በ2013 ዓ.ም 6 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ማቀዷ ይታወሳል።

ችግኞቹን ለማፍላት የሚውል በ6 ክልሎች 100 ሚሊዮን ብር መመደቡን የፌደራል አካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ጋሻው ለኢቲዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ እንዳሉት በዘንድሮው አመት እቅድ ውስጥ ከሌሎች አመታት በተለየ 6 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የታቀደ ሲሆን 1 ቢሊዮን ችግኙን ጎረቤት አገራትን ባሳተፈ መንገድ ለመትከል መታቀዱን ተናግረዋል።

ይሄም ያስፈለገበት ለምስራቅ አፍሪቃ ይሄ መነሳሳት እንዲስፋፋ እና መልካም ግንኙነትን ለመፍጠር ይረዳ ዘንድ እንደሆነም አንስተዋል፡፡

ይሄን እቅድ ለማስተግበር ይረዳ ዘንድ ችግኞቹ ተፈልተው እንዲዘጋጁ የሚደረግበት ቦታ ከአገራቶቹ አዋሳኝ ድምበር ላይ መሆኑንም ተጠቁሟል፡፡

በዚህም ለሱዳን መተማ ጋር ፣ ለጅቡቲ ሆለታ ላይ፣ ለሶማሊያ ድሬዳዋ እና ሃረር አካባቢ ሲሆን ለኤርትራ ደግሞ በሰሜን ኢትዮጲያ አካባቢዎች ላይ ችግኞች ተፈልተው እንደሚዘጋጁ አቶ ተስፋዬ ጠቁመዋል ፡፡

በተያያዘም ችግኝ በማፍላት ሂደት ውስጥ በጥምረት ከምርምር ተቋማት ጋር እና ከ10 ዩኒቨርሲዎች ጋር እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ስራ ውስጥ 6 ክልሎች ተመርጠው፤ተቋማችን በፋይናንስ እና በአቅርቦት ይደግፋቸዋል ፤ የምርምር ተቋሞቹ ደግሞ በቴክኖሎጂ በየ ክልሎቹ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጀት ተመድቦ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎቹም ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፣ሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ፣ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ፣ ድሬዳዋ እና ጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ ይሳተፋሉ ብለዋል።

በረድኤት ገበየሁ
ጥር 6 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *