የሀገር ውስጥ ዜና

የአዲስ አበባ አዳማ እና ድሬዳዋ ደወሌ ፍጥነት መንገድ ባለፉት ሰድስት ወራት ውስጥ ከ193 ሚሊዮን በላይ ብር ገቢ አስገኘ።

ኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቀው የአዲስ አበባ-አዳማ እና ድሬዳዋ-ደወሌ ፍጥነት መንገድ በ2013 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከ 193 ሚሊየን 385 ሺህ ብር ገቢ አስገኝቷል፡፡

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያልተቋረጠ የ24/7 አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

አገልግሎቱን ያለማቋረጥ የሚሰጠው ይህ ተቋም ቀልጣፋና ዘመናዊ በሆነ መልኩ የተጠቃሚዎቹን ፍላጎት ለማሟላት የተለያዩ ተግባራትን ሲከውን ቆይቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ በአዲስ- አዳማ እና በድሬዳዋ- ደወሌ የክፍያ መንገዶች 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን የትራፊክ ፍሰት ለማስተናገድ ታቅዶ 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ፍሰት ተከናውኗል።

በተጨማሪም ከክፍያ መንገድ አገልግሎት ብር 194 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 180 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል፡፡

እንዲሁም ከልዩ ልዩ ገቢዎች (ከማስታወቂያ ቦታዎች ኪራይ፣ ከወደሙ የመንገድ ሃብቶች ካሳ ክፍያ፣ ከተሽከርካሪ ማንሻና መጎተቻ…) ብር 12 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በማከል በአጠቃላይ 193 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ኢንተርፕራይዙ ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታውቋል።

በድሬደዋ- ደወሌ የክፍያ መንገድ የተሽከርካሪዎች የክብደት ቁጥጥር ስራ ውጤታማ አለመሆኑ እና ከክብደት በላይ ጭነው የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች በመንገዱ ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑ ትኩረት የሚሻ ጉዳዮች መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

በዳንኤል መላኩ
ጥር 6 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *