የኢትዮጲያ መስማት የተሳናቸው ማህበር የ45 ዓመት ጥያቄው እንደተመለሰለት አስታወቀ።

መስማት የተሳናቸው ዜጎች አሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ገብተው የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና መውሰድ ሊጀምሩ ነው፡፡

የመጀመሪያ ዙር ስልጠና ከጥር 16 ጀምሮ የሚሰጥ መሆኑን ኤትዮ ኤፍ ኤም ከኢትዮጲያ መስማት የተሳናቸው ማህበር ሰምቷል፡፡

ይህንን ጥያቄ ማህበሩ ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 45 ዓመታት ሲጠይቀው የነበረው መሆኑን የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ትዕግስት ዓለማየሁ ገልፀዋል።

ኢትዮጲያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን የአካል ጉዳተኞችን መብት ኮንቬንሽን ከፈረሙ ሀገራት መካከል እንደመገኘቷ አካል ጉዳተኞች ያለአንዳች አድሎ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተጠቃሚዎች ይሆኑ ዘንድ ዋስትና የመስጠት ግዴታ ተጥሎባታል፡፡

በመሆኑም መስማት የተሳናቸው ዜጎች አሰፈላጊውን ስልጠና በመውሰድ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ማግኘት እንዲችሉ የአሰራር ማንዋል ሲዘጋጅ መቆየቱን የኢትዮጲያ መስማት የተሳናቸው ማህበር ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ትዕግስት ዓለማየሁ ለኤትዩ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

መስማት የተሳናቸው ዜጎች የማሽከርከር መብታቸው ተረጋግጦ የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገት ቀጣይና ዘላቂ እንዲሆን የራሳቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ማድረግ እና ማሽከርከር አይችሉም በሚል የተሳሳተ አመለካከትና ግንዛቤ የሚፈጥረውን የስራ አጥነት ችግር በመቅረፍ ወደ አምራች ዜጋ መቀየር የጥረታችን ዋና አላማ ነው ብለዋል ወ/ሮ ትዕግስት፡፡

ስራ አስኪያጇ አክለውም በሀገራችን የህግ ማእቀፎችን በማሻሻል መስማት የተሳናቸው ዜጎች ባላቸው እውቀትና ችሎታ በማንኛውም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳታፊነታቸውን ለማረጋገጥ እየተሰራ ይገኛል፡፡

በዚህ መሰረት የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ አዋጅ 1074/2010 መሰረት በማድረግ መስማት የተሳናቸው ሰዎች አሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ገብተው የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና በመውሰድ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ማግኘት እንዲችሉ የአሰራር ማንዋል ተዘጋጅቷል፡፡

ማህበሩ ከትራንስፖርት ሚኒስትር ፣ ከጤና ሚኒስትር ከትራፈክ ፖሊስ ፅ/ቤት እና ከሰራተኛና ማህበራዊ ጎዳይ ጋር በመሆን እየሰራ መሆኑን አንስተው ከዚህ በፊት በጤናው ዘርፍ ምርመራ ሲደረግ በጆሮ አካባቢ ችግር ካለ የይለፍ ወረቀት አይሰጥም ነበር።

አሁን ግን ጤና ሚኒስትር ይህንን ለጤና ተቋማት በሙሉ ማሰረጃ እንዲሰጥልን እንዲሁም ደግሞ የትራፊክ ፖሊስ ፅ/ቤት ይህ መረጃ እንዲኖረው ለማድረግ ጊዜ ቢወስድብንም ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ስልጠናው ይጀመራል ተብሏል፡፡

በያይኔአበባ ሻምበል
ጥር 6 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.