የሴቶች መደፈር፣ ግድያ ፣ ዝርፍያ ፣ እና ሌሎች ወንጀሎች የሚሸሸጉበት አዲሱ አደይ አበባ ስታዲየም

አቶ ፈለቀ አጥናፌ ይባላሉ የ76 አመት የዕድሜ ባለፀጋ ናቸው፡፡ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 አዲሱ አደይ አበባ ስቴድየም አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ ስታዲየሙ ውስጥ በሚመሸጉ ሌቦች በደረሰባቸው ጉዳት ከአገር ውስጥ እስከ ውጪ ሆስፒታሎች ተመላልሰው ህክምና ተከታትለው አሁን መጠነኛ ለውጥ ማሳየታቸውን ይናገራሉ፡፡

ከ30 አመት በላይ ኖረዋል፡፡ ክፉ ደጉን ባየንበት እንቅስቃሴያችን ሁሉ በፍርሀት በሰቆቃ ሆነ፣ ሰላምና አጣን፤የመኖር ዋስትናችን ተነጠቀ ብለዋል፡፡ ወደ ሰፈሩ ስንመጣ ቦታው ባዶ ስለነበር የምንፈራው ጅብ ነበር፣ አሁን ደግሞ ያኔ ጅቡን ከምንፈራው በላይ የምንፈራው ሰው ነው ይላሉ::

ከውጪ የመጣች ዘመዳቸው ፤ ሀገር ቤት የገባች ቀን መዘረፏን የነገሩን አቶ ፈለቀ፤ እኔንም በቃ ገለነዋል ብለው የወሰዱብኝን ሞባይል ይዘው የዘመዴንም የልጆቿንም ፓስፖርት የያዘውን ቦርሳ ይዘው የገቡት ወደ ስታዲየም ነው ብለዋል፡፡ በአካባቢው የጭፈራና የሺሻ ቤቶች እንቅልፍ ማጣታችን ሳያንስ የማያልቀው ስታዲየም ለሌቦቹ መመሸጊያ በመሆን የመኖር ዋስትናችን ነጠቀን ሲሉ ምሬታቸውን ገልፀዋል፡፡

ሌላው በአካባቢው ባለ አራት ወለል ያለው ህንጻ ቤት ሰርተው እያከራዩ የሚኖሩት አቶ መሰከረ ረታ፤ በአካባቢው በተንሰራፋው ሌብነት ምክንያት ፤ተከራዮች ዘራፊዎቹን ፈርተው በመልቀቃቸው ቤቴ ከተከራየ 1 አመት ከ 6 ወር አለፈው ብለውናል፡፡ግዙፎቹ የቻይና ቴሌኮም ኩባንያዎች ሁዋዌና ዜድ ቲ ኢ ፤ ቤቴን ተከራይተውት ነበር ያሉ ሲሆን ሁለቱም በዘረፋ ተሰላችተው ለቀው ሄደዋል ብለዋል፡፡

በአካባቢው ወደ ሚገኘው ቻይና ሬስቶራንት የሚመጡ የውጪ ዜጎችን መዝረፍ ብቻ ሳይሆን ተሰብስበው ይደበድባሉ ብለዋል፡፡የአካባቢው ነዋሪዎች፣ስራቸው በዚያው አካባቢ የሆነ እንዲሁም በአዲሱ አደይ አበባ ስቴዲየም አካባቢ ሲያልፉ የተዘረፉ ሰዎች ብሶታቸውን ለጣቢያችን ያጋሩን ሲሆን ሁሉም ወንጀለኞቹ ከዘረፉን በኋላ ወደ ስታዲየም ነው የሚገቡት ብለዋል፡፡

ከጓደኛዋ ጋር በቅርቡ ወደ ገባንበት በአካባቢው ወደ ሚገኘው ቢሮዬ እየሄድኩ ነበር የምትለው ደግሞ መስከረም ነች፡፡ ሁለት ሆነው መጥተው ስልኬን በግድ ታግለው ተቀበሉኝ ፤ ጓደኛዬ በዣንጥላዋ ለመከላከል ሞከረች፣ ግን አልተሳካም ስትል በቁጭት ተናግራለች፡፡

በጣም የገረመኝ ትላለች መስከረም፤ በጣም የገረመኝ ፤ ከሰረቁን በኋላ ምንም እዳልተፈጠረ፣ የራሳቸውን ንብረት ተቀብለው እንደሚሄዱ ሁሉ ዘና ብለው ነው ወደ ስታዲየም የገቡት ያለች ሲሆን በጣም ብዙ ሰው የሆነውን እያየ ዝም ማለቱ ለራሳቸው ደህንነት በመስጋታቸው እንደሆነ ነግራናለች፡፡

በአዲሱ ስታዲየም አካባቢ እያለፈ የነበረው ናሆም ደግሞ በመንገድ መዘጋጋት ምክንያት መኪናው ውስጥ ተቀምጦ ረዘም ላለ ጊዜ መንቀሰቀስ ባለመቻሉ አዲስ አይፎን ስልኩ የሌቦች ሲሳይ መሆኑን በሀዘኔታ አጫውቶናል፡፡

አንድ ልጅ መጣና የመኪናውን ስፖኪዮ በሀይል መቶ አጠፈው፤ እኔ በንዴት ጦፌ ትኩረቴን ወደሱ በማድረግ ምን መሆኑ እንደሆነ ስጠይቀው፤ለካ ጓደኛው ክፍት በነበረው በሌላኛው የመኪናው መስኮት ስልኬን ይዞ እየሮጠ ነበር ብሏል፡፡ተከትየው ወደ ገባበት ስታዲየም ልገባ ስል ፤ አብደህ ካልሆነ እንዳታደርገው፣ ተደብድበህ ሌላ እቃም አስረክበህ ነው የምትወጣው አሉኝ ፣ ስለዚህ ስልኬን አስረክቤ ተመለስኩ ብሎናል፡፡

ስሟን መጥቀስ ያልፈለገችው በአካባቢው ተወልዳ እንዳደገች ያነገረችን ወጣት ደግሞ ፤ ሁልጊዜም የአካባቢው ሰዎች ሌቦች እየተከተሉሽ ነው፣ ተጠንቀቂ ስለሚሉኝና በሌሎች ላይ የሚደርሰውን ዝርፊያ ስለማውቅ በጣም ነበረ የምጠነቀቀው ያለች ሲሆን የስራ ሰርቪስ ልይዝ ከቤት በወጣሁበት አንድ ጠዋት ግን የሌሎቹ ክፉ ዕጣ እኔ ላይም ደርሷል ብላናለች፡፡

መሬት ላይ በጭንቅላቴ ፈጥፍጦኝ ቦርሳዬን ይዞ አላልቅ ወዳለው አደይ አበባ ስታዲየም ገባ ብለለች፡፡ ሆስፒታል በመሄድ ጭቅላቴ ላይ የደረሰው ጉዳት የከፋ እንዳልነበረ ባውቅም ከዚያ በኋላ ኑሮዬ ሁላ የፍርሀትና የሰቆቃ ሆነ ስትል ህግና መንግስት ባለበት ሀገር መሀል ከተማ ላይ በጭንቀት መኖሯ እንደሚያንገበግባት ነግራናለች፡፡ሰፈሩ እኮ የለየለት የውንብድና ሰፈር ሆኗል የሚሉት እነዚህ ሰዎች ስታድየሙ መቼ ነው የሚያልቀው? እንዴት ስቴዲየሙስ የሌቦች መመሸጊያ ሲሆን መንግስት ዝም ብሎ ያያል? ሲሉ ትዝብታቸውንና ጉዳታቸውን አጋርተውናል፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 በተለምዶ ሀያ አምስቱ አፓርትማ ተብሎ በሚታወቀው መንደር ውስጥ የሚኖሩ 450 እና ከዚያ በላይ የሆኑ አባወራዎች ለስፖርት ኮሚሽን፣ ለወረዳ፣ ለክፍለ ከተማ እና ለከተማ አስተዳደሩ ስቃያቸው እንዲቆምላቸው ተደጋጋሚ አቤቱታ አስምተዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ለጣቢያችን እንተናገሩት በነዚህ ወንበዴዎች ምክንያት ሴቶች ይደፈራሉ፣ህፃናት ወንዶች ላይ ጥቃት ይደርሳል፣የውጪ ዜጎች ሳይቀር ይደበደባሉ፣ እስከ ሞት አደጋ የደረሰበትም አለ ሲሉ ነግረውናል፡፡በመኖርያ ቤቶች ላይ በተገጠሙ ካሜራዎች ዝርፍያ ሲፈፀም የተቀረፁ ቪዲዮዎች ነዋሪዎቹ ለጣቢያችን የላኩ ሲሆን ሌቦቹ ለመዝረፍ ከአደይ አበባ ስታዲየም ሲወጡ፣ ከነጠቁ በኋላ ደግሞ ወደ ስታዲየሙ ሮጠው ሲገቡ ቪዲዮው ያሳያል፡፡

በስፖርት ኮሚሽን የስፖርት ፋኩልቲ ዳይሬክተር አቶ አስመራ ግዛው ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት ፤ እኛም ተቸግረናል፣ ጥበቃ እየተደበደበ የሳይቱ ዕቃ እየዘተረፈ ነው ፣ ነዋሪዎቹ ለኛ ደብዳቤ ፅፈዋል፣ እኛ ደግሞ ክፍለ ከተማ ደብዳቤ ፅፈናል ብለዋል፡፡ዋናው ችግር የሆነብን በህገ ወጥ መንግድ በቦታው ሸራና ላስቲክ ወጥረው የሚኖሩት ናቸው ያሉ ሲሆን ከተፈቀደ በር ውጪ መስጊድ አለ፣ በመስጊዱ በኩል ደግሞ ፤ ሌላ በር አለ፣ በዚያ በኩል ነው የሚገቡት እሱን ለመቆጣጠር ደግሞ በፍርድ ቤት ሂደት ላይ ያለው መስጊድ ሌላ ምትክ ቦታ ማግኘት አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ሳይጀመር ጀምሮ ባለፈው ሳምንት ፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት እስከተደረገው የምክር ቤት ጉባኤ ድረስ ይሄን ጉዳይ ሺህ ጊዜ ጠይቀናል ፤ ያሉ ሲሆን ክፍለ ከተማው ለመስጊዱ ምትክ ቦታ እፈልጋለሁ ብሏል ሲሉ የነገሩን ሲሆን ፖሊስ ያኔ ህገ ወጥ ሰፋሪዎችን አጸዳለሁ ብሏል ብለውናል፡፡

ስታዲየሙ በፕሮግራሙ መሰረት እየተሰራ ነው የሚሉት አቶ አስመራ አንደኛው ምዕራፍ አልቆ ሁለተኛው የማጠቃለያ ምዕራፍ ተጀምሯል፤ የሚመለከተው ክፍል ህገ ወጥ ሰፋሪዎቹን ካላነሳልንና ለመስጊዱም ሌላ ምትክ ቦታ ካልሰጠ ግን ነዋሪው ላይ ብቻ ሳይሆን ፕሮጀክቱ ላይም ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር ሄደን ስለ ጉዳዩ ጠይቀናቸዋል፡፡ የተለየ ትኩረት ሰጥተን የምነከታተከውና የምንጠበቀው ቦታ ነው ሲሉ ነግረውናል፡፡

በኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ በህገ ወጥ መንገድ ሸራና ላስቲክ ወጥረው የሚኖሩት ካልተነሱ ችግሩ ዘላቂ መፍትሄ አያገኝም ያሉ ሲሆን የሚመለከተው አካል ይሄን እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ ጭፈራና ሺሻ ቤቶች ለችግሩ መበርከት ሌላ ምክንያት እንደሆኑም ገልፀዋል፡፡

ከወንጀለኞቹ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ከነዚሁ ዲስኮ ቤቶች የሚወጡ ረጅም እጅ ያላቸው ሰዎች ጥቂት አይደሉም ብለዋል፡፡በቋሚነት ከተመደቡ ፖሊሶች በተጨማሪ ቦታው አደገኛ በመሆኑ ምክንያት በየትኛውም የአዲስ አበባ ክፍል ያላደረግነውን በቋሚነት ፓትሮል መኪና እየተሸከረከረ እንዲጠብቅ መድበናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ሄዶ መፍትሄ ያላገኘው መስጊድና የአየር ካርታ ጭምር አለን በማለት ከቦታው አንነሳም የሚሉ ሕገ ወጥ ሰፋሪዎቹን የሚመለከተው ክፍል መፍትሄ ካላበጀላቸው ግን የአካባቢው ችግር ዘላቂ መፍትሄ አያገኝም ብለዋል፡፡

ተለዋዋጭ ባህሪ ያውን በከተማዋ የተንሰራፋውን ስርቆት ለመቀነስ በግጭትና በተለያዩ ምክንያቶች ወደ መዲናዋ የሚፈልሱት ወጣቶች ላይ እልባት መሰጠት አለበት የሚሉት ኮማንደር ፋሲካ ህዝቡም የስርቆት ወንጀል ሲፈጸምበት አንዴ አመልክቶ ምላሽ ካላገኘ ወደ በላይ አካል ሄዶ ጉዳዩን የማስፈፀም ልምድ ማዳበር አለበት ሲሉ ምክራቸው ለግሰዋል፡፡

በስቴዲየሙ ዙርያ በህገ ወጥ መንገድ ስለሚኖሩት፣ስለሚነግዱትና፣ ምትክ ቦታ ይፈልግለታል ስለተባለው መስጊድ ልንጠይቅ ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡

በሔኖክ አስራት
ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.