የተባበሩት አረብ ኢምሬት በሰራተኛ ቅጥር ዙሪያ ያሳለፈችውን ውሳኔ ኢትዮጵያ እንደምትቀበለው አስታቀች።


የተባበሩት አረብ ኢምሬት በአገሯ ሰራተኞችን ከተለያዩ የዓለማችን አገራት መቅጠር የሚያስችሉ ሶስት አይነት የአሰሪ እና ሰራተኛ ህጎች አሏት።

ከነዚህ ሶስት አይነት ህጎች ውስጥ በኤጀንሲዎች የሚፈጸሙ የአሰሪ እና ሰራተኛ ህጓን ባሳለፍነው ሳምንት መሰረዟ ይታወሳል።
በዚህ የስራ ዘርፍ 250 ቀጣሪ ተቋማት ሰራተኞችን ከተለያዩ የዓለማችን አገራት ይቀጥሩ የነበሩ ሲሆን አሁን ሁሉም ስራቸውን ከአንድ ወር በኋላ ያቆማሉ።

ይህ የሰራተኞች ቅጥር ከተለያዩ አገራት የቤት ሰራተኞችን ወደ ተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በቀጣሪ ኤጀንሲዎች አማካኝነት በማምጣት ለሰራተኛ ፈላጊ የአገሬው ዜጎች የሰው ሃይል ይቀርብ ነበር።
አገሪቱ ይሄንን በኤጀንሲዎች አማካኝነት የሚፈጸም ቅጥርን የሚተካ መንግስታዊ ተቋም በማደራጀት ቅጥሩን እንደምታከናውን አስታውቃለች።

በዚህ የቅጥር አይነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ ዱባይ እና ሌሎች የአገሪቱ ከተሞች በማምራት በመስራት ላይ ይገኛሉ።
በርካቶችንም ወደዚያው ለማምራት የኮቪድን መጥፋት በመጠባበቅ ላይ ናቸው።
ኢትዮ ኤፍ ኤም ይህ የተሰረዘው ህግ ኢትዮጵያዊያንን ይጎዳ ይሆን ሲል? የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠይቋል።

በሚኒስቴሩ የህገወጥ ሰራተኛ ምልመላ መከላከያ ቡድን መሪ አቶ ዘሪሁን የሺጥላ እንዳሉት የተባበሩት አረብ ኢምሬት የሰረዘችው ህግ ላለፉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያዊያን ሲጠቀሙበት የነበረ ህግ ነው ብለዋል።
ይሁንና በኤጀንሲዎች አማካኝነት የሚፈጸመው የሰራተኛ ቅጥር ብዙ ኢትዮጵያዊያንን ለእንግልት እና ለጉዳትም የዳረገ በመሆኑ ህጉ መሻሩ ኢትዮጵያዊያንን ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም ሲሉ አቶ ዘሪሁን ተናግረዋል።

የተባበሩት አረብ ኢምሬት ይሄንን ህግ በመሻር ስራውን ከኤጀንሲዎች ይልቅ በመንግስት ተቋም እንዲፈጸም አቅጣጫ ማስቀመጧ ኢትዮጵያዊያንን የበለጠ ደህንነቱ የተረጋገጠ ስራ እንዲሰሩ ያደርጋልም ብለዋል።

ችግሮች ሲፈጠሩም የኢትዮጵያ መንገስት በቀጥታ ከተባበሩት አረብ ኢምሬት አቻ ተቋማት ጋር በመነጋገር መፍትሄ እንዲፈልጉ እንደሚያደርግም አቶ ዘሪሁን ተናግረዋል።
በሳሙኤል አባተ
ጥር 17 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *