ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ብቻ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ1 ቢሊዮን በላይ ብር ድጋፍ መደረጉ ተገለጸ።

የታላቁ ህሳሴው ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቀው ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ብቻ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ1 ቢሊዮን በላይ ብር ድጋፍ ተደርጓል።

የጽ/ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሃይሉ አብርሃም እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን መገንባት ከጀመረች ወዲህ ለግድቡ ግንባታ መሳካት መላው ኢትዮጵያዊያን ያደረጉት ድጋፍ ከፍተኛ ነው።

ከሃምሌ 1 እስከ ታህሳስ 30 2013 ዓ.ም ድረስ ባሉት 6 ወራት ውስጥ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ቦንድ ግዢና ከሌሎችም ገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶች 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል።

ድጋፉ እስከዛሬ ድረስ ከተደረጉት በጣም ከፍተኛው ሲሆን ይህም በ6 ወር ብቻ የተሰበሰበው ብር ካምናው 2012 በጀት አመት ከተሰበሰበው 747 ሚሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ250 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥ 416 ሚሊዮን ከዳያስፖራው ቦንድ ግዢና በስጦታ የተሰበሰበ ሲሆን፣ 66.9 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ደግሞ በ8100 A አጭር የሞባይል መልእክት የተሰበሰበ መሆኑን አብራርተዋል።

መላው የሃገራችን አርሶ አደርና አርብቶ አደርም ለግድቡ ግንባታ ዙሪያ በጉልበቱ የሰራው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ደግሞ በገንዘብ ሲሰላ ወደ 120 ሚሊዮን የሚጠጋ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።

አቶ ሃይሉ በጠቅላላው ግድቡ በይፋ ከተበሰረበት መጋቢት 24/ 2003 ዓ.ም ጀምሮ ለግድቡ ግንባታ ተሰብስቦ ገቢ የሆነው ከ14.7 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ገልጸዋል።

በጅብሪል ሙሀመድ
ጥር 19 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *