ከኦሮሚያ ክልል፤ ከትግራይ ክልል፤ ከደቡብ ክልል፤ እና ከቤኒሻንጉል ክልል በተፈጠሩ የተለያዩ ግጭቶች ምክንያት ለደህንነታቸው ሰግተው ወደ አማራ ክልል የገቡ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ኢትዮ ኤፍ ኤም ሰምቷል፡፡
በምእራብ ጎጃም፤ሰሜን ሸዋ ፣ሰሜን ወሎ ፤ራያ ቆቦ፤ እና በሌሎችም የክልሉ ቦታዎች ባሉ መጠለያ ጣቢያዎች ከ270 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ይገኛሉ ተብሏል፡፡
የክልሉ አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባባሪያ ኮምሽን ምክትል ኮምሽነር ወ/ሮ እታገኘው አደመ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቁት የተፈናቃዮች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ይገኛል፡፡
በክልሉ በአብዛኛው በምእራብ ጎጃም ተጠልለው የሚገኙ ዜጎችም ከመተከል ተፈናቅለው የመጡ ተፈናቃዮች መሆናቸውንም ነግረውናል፡፡
ለተፈናቃዮች የቀለብና የተለያዩ ድጋፎችን ለማሰባሰብ እና ለማቅረብ ከማህበረሰቡ፤ከሃይማኖት ተቋማት፤ ፤ከንግድ ማህበረሰብ እንዲሁም ከፌደራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን ድጋፉን ለተፈናቃዮች እየቀረብን ነው ብለዋል።
ይህንና አልፎ አልፎ የመቆራረጥና በቂ አቅርቦት ያለመኖር ችግር እንደሚያጋጥም ነግረውናል፡፡
እንደ ክልሉ አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባባሪያ ኮምሽን ከሆነ እነዚህን ዜጎች ለመደገፍ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ወደ ቀደመ ቀያቸው መመለስ ያስፈልጋል ብለዋል።
በየውልሰው ገዝሙ
ጥር 24 ቀን 2013 ዓ.ም











