በአማኑኤል የአዕምሮ ጤና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኤሌክትሪክ ንዝረት ህክምና ዳግም መስጠት መጀመሩን ተናግሯል።
በሆስፒታሉ የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ዮናስ ላቀው የኤሌክትሪክ ንዝረት ህክምናው መጀመሩን ለኢትዮ ኤፍ ኤም አረጋግጠው ከባድ የድብርት ህመም ላለባቸው ተደጋጋሚ ራስን የማጥፋት ሀሳብ ላላቸው ሰዎችና አልበላም አልጠጣም አልናገርም ለሚሉ ሰዎች የኤሌክትሪክ ሀይል በመልቀቅ አንጎላቸውን የምናነቃበት ህክምና ነው ብለውናል።
የኤሌክትሪክ ንዝረት ህክምና በኢትዮጵያ በተለይም በአማኑኤል የአዕምሮ ጤና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከተጀመረ ወደ 20 አመት እንደሚጠጋ ይነገራል።
በአማኑኤል ሆስፒታል ብቻ የሚገኘው ህክምናው ከመላው የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚመጡ ታካሚዎችን እንደሚያስተናግድም ሰምተናል።
ህክምናውን ለማድረግ የሚሰጥ ማደንዘዣ ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር ላይሄድ ይችላል በሚል አገልግሎቱ ተቋርጦ እንደነበረ የነገሩን ዶክተር ዮናስ ላቀው አሁን ላይ ግን የኤሌክትሪክ ህክምና ክፍሉም ጽዳትና እድሳት ተደርጎለት ዳግም ስራ ጀምሯል ብለውናል።
ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞም ታካሚዎች ሲመጡ ቅድሚያ የኮቪድ ምርመራ ተደርጎላቸው ህክምናውን ያገኛሉ ሲሉ ተናግረዋል።
በመቅደላዊት ደረጀ
ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም











