የቆዳ ኢንደስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ከ17 ሚሊየን በላይ ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።

በ2013 በጀት አመት በ6 ወራት ውስጥ ኢንስትቲዩቱ 17.7 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ገልጿል።

የኢንስቲትዩቱ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብርሀኑ ሰርጃቦ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት ካለቀለት ቆዳና ከቆዳ ነክ ምርቶች 11.9 ሚሊዮን ዶላር ከጫማ 3.1 ሚሊየን ዶላር ከጓንት 2.1 ሚሊየን ዶላር ከአልባሳትና ከዕቃዎች ደግሞ 2.8 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን አብራርተዋል።

በዚህም ለማሳካት ከተያዘው ዕቅድ ጋር ሲተያይ 63.5 በመቶ ማሳካት ተችሏል
ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም እጅግ ዝቅተኛ ገቢ እንደተገኘ አቶ ብርሀኑ ነግረውናል።

ለእቅዱ ማነስ ዋነኛው ምክንያትም ኮቪድ 19 ነው ተብሏል።

በ2012 ዓ.ም በ6 ወር ውስጥ 49.5 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቶ እንደነበረ ያስታወሱት አቶ ብርሀኑ በዚህ አመት ግን በወረርሽኙ ምክንያት የአለም ገበያ ዝግ በመሆኑ በሚፈለገው መልኩ ቆዳና የቆዳ ምርቶችን መሸጥ አልተቻለም ብለውናል።

የቆዳና ሌጦ የጥራት ችግር አሁንም ባለመቀረፉ ሌላኛው እንቅፋታችን ነበረ ሲሉ ተናግረዋል የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ብርሀኑ።

የቆዳ ኢንደስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት በሞጆ የቆዳ ጥራት ላቦራቶሪ እየገነባ እንደሆነ ማሳወቁ ይታወሳል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያን የቆዳ ምርቶችን ለአለም ሀገራት በሚገባ እያስተዋወቀ መሆኑንም ከኢንስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

በመቅደላዊት ደረጀ
ጥር 26 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.