ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ታይቶ የማያውቅ አኖፊለስ ስቴፈንሲ የተሰኘ የወባ ትንኝ ተገኝቷል።
ይህ አዲስ ትንኝ በአሁን ሰአት የወባ ማጥፊያ የተባሉ ኬሚካሎችን የመቋቋም አቅም ስላለው አስቸጋሪ ያደርገዋል።
በከፍተኛ ሁኔታም እንደሚተላለፍም ተገልጿል።
አርማውር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ባጠናው ጥናትም የወባ ትንኙ በይበልጥ የሚራባው ከተማ አካባቢ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በሶማሌ ክልል ቀብሪዳሀር እንደሆነም ኢንስቲትዩቱ ገልጿል ።
ይህ አዲስ ትንኝ በምስራቅ ኦሮሚያ እስከ ዝዋይ ድረስ ተስፋፍቷል።
አሁን ባለው መረጃ በ13 የኢትዮጵያ ከተሞች የወባ ትንኟ ተገኝታለች ተብሏል።
ትንኙ ኤዢያ ውስጥ የነበረች ትንኝ ወደ ኢትዮጵያ በመግባቷ እንደሆነ ተገልጿል።
ይህን አዲስ ትንኝ ጸረ ትንኝ ኬሚካል ሊበግረው ባለመቻሉ በኢትዮጵያ ሊደርስ የሚችለውን ተፅዕኖ ለማስቀረት የምርምር ስራው በተጠናከረ መልኩ እንደቀጠለ አጥኚው ቡድን በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
በጅቡቲ በ2012 ይቺው የወባ ትንኝ መገኘቷ የተገለጸ ሲሆን በዚህም የጅቡቲ የወባ ተያዥ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ኢትዮጵያም የመከላከል ስራዋን መጀመር አለባት የሚለውን አንስተዋል።
በመቅደላዊት ደረጀ
ጥር 27 ቀን 2013 ዓ.ም











