አሜሪካ ለየመን ጦርነት የምታደርገውን ድጋፍ ልታቆም ነው።

አሜሪካ በየመን ለስድስት አመት የተካሄደውንና ከ 110 ሺህ በላይ ሰዎች የሞቱበትን ጦርነት መደገፍ ላቆም ነው ብላለች፡፡

ይሄ የፖሊሲ ለውጥ በአዲሱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አማካኝነት ነው የተገለፀው፡፡

በየመን የሚገኘውን አማፂ ቡድን ሀውቲ፤ እየተዋጋ ያለውን በሳኡዲ አረቢያ የሚመራውን ጥምር ሀይል ከባይደን በፊት የነበሩት ሁለት ፕሬዝዳንቶች ከመሳርያ አቅርቦት አንስቶ በተለያዩ መንገዶች ሲረዱ ከርመዋል፡፡

እንደ አውሮፓውያኑ በ 2014 ነበር በየመን መንግስት ላይ የሀውቲ የአመፅ ንቅናቄ ሚሊዮኖችን ለረሀብ የዳረገውን ጦርነት የቀሰቀሰው፡፡

ጦርነቱ የከፋው ከአንድ አመት በኋላ ሳኡዲ አረቢያ እና ሌሎች ስምንት የአረብ ሀገራት በአሜሪካ፣በእንግሊዝ እና በፈረንሳይ እየተደገፉ የሀውቲ አማፅያንን በአየር መደብደብ ሲጀምሩ ነበር፡፡

የሀውቲ አመፅያን ደግሞ በኢራን ይደገፋሉ፡፡

በአሁን ሰአት ሰማንያ በመቶ ወይንም 24 ሚሊዮን የመናውያን ሰብአዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ 12 ሚሊዮኑ ህፃናት ናቸው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በሔኖክ አስራት
ጥር 28 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *