በትግራይ ክልል ስራ አቁመው ከነበሩ 40 ሆስፒታሎች ውስጥ 15ቱ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ መመለሳቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ አንዳሉት በክልሉ በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት አቁመው የነበሩ ጤና ተቋማት ወደ አገልግሎት እየተመለሱ ነው፡፡

እስካሁን በተደረገው ድጋፍ እና ክትትል የመድሀኒትና ግብአት ስርጭት ተደርጎ ወደ ስራ የገቡ ጤና ተቋማት 88 መድረሳቸውንም ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።

በክልሉ በአምስቱም ዞኖች ካሉት 40 ሆስፒታሎች ውስጥ 15 ሆስፒታሎች ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገቡ 5ቱ ደግሞ በከፊል አገልግሎት እየሰጡ ነው።

እንዲሁም በክልሉ ካሉት 224 ጤና ጣቢያዎች 68 ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉም ብለዋል፡፡

ሌሎች ሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎች በአጭር ጊዜ ወደ አገልግሎት ለመመለስ እና የጤና አገልግሎቶችን ለሕዝቡ ተደራሽ ለማድረግ የጤና ሚንስቴር፤ ኤጀንሲዎቹ እና የጤና ቢሮ ከአጋር ድርጅቶች ጋር እየሰሩ መሆኑን ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።

ተቋማቱን ወደ አገልግሎት ለመመለስ የሚያስችሉ መድሀኒቶች እና የህክምና መገልገያዎች የሚያሰራጩ የመቀሌ እና የሽሬ የመድሀኒት አቅርቦት ቅርንጫፎች የግብዐት ስርጭት እንዲፋጠን በሙሉ አቅማቸው እየሰሩ ነው ተብሏል።

እነዚህ ተቋማት ወደ አገልግሎት ሲገቡ የደም አቅርቦት ላይ ችግር እንዳይፈጠር በክልሉ የሚገኙትን የደም ባንኮች ወደ ስራ ማስገባት ተችሏል፡፡

በክልሉ በሚገኙ ደም ባንኮች ለማይሸፈኑ ፍላጎቶች ደግሞ ከአዲስ አበባ ደም እየተላከ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮጵያዊያን
የካቲት 4 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.