በትግራይ ክልል ባለፉት 60 ቀናት ውስጥ ብቻ 108 የአስገድዶ ደፈራ ወንጀሎች መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ከጥር 2 ቀን እስከ ጥር 15 ቀን 2013 ዓ.ም. በመቀሌ ከተማ እና በደቡባዊው የትግራይ ዞን አላማጣ፣ መሆኒ እና ኩኩፍቶ ከተሞች ክትትል እና ምርመራ በማድረግ፣ በተለይም በመቀሌ የሚገኙ ከፍተኛ ወታደራዊ እና ሲቪል አመራሮችን፣ የጤና ዘርፍ ሰራተኞችን፣ ነዋሪዎችን፣ ተጎጂዎችን እና ተፈናቃዮችን አነጋግሬያለሁ ብሏል።

ኢሰመኮ ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ በትግራይ ክልል መቀሌን ጨምሮ በአራት ሆስፒታሎች በተገኘ መረጃ መሰረት ባለፉት 60 ቀናት ውስጥ ብቻ 108 የአስገድዶ ደፈራ ወንጀሎች ተፈጽመዋል።

እንዲሁም በመቀሌ እና የኢሰመኮ ክትትል ቡድን በተዘዋወረባቸው አካባቢዎች የሰብአዊ እርዳታ በማዳረስ ረገድ አበረታች እርምጃዎች አሉ ብሏል።

ይሁንና አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎቱ አሁንም አልተሟላም ያለው ኮሚሽኑ ከሌሎች የትግራይ ክልል አካባቢዎች ወደ መቀሌ የተፈናቀሉ ሰዎች የምግብ፣ የንጹሕ መጠጥ ውሃ እና የጤና አገልግሎት አቅርቦት እጥረት አለባቸው።

በተለይም በሌሎች የትግራይ ክልል አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ሁኔታ እና የጤና ተቋማት አገልግሎት መቋረጥ፣ ተጎጂዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች የህክምና እርዳታ ለማግኘት ረዥም የእግር መንገድ እንዲያደርጉ አስገድዷል።

ኢሰመኮ በአይደር ሆስፒታል የሕፃናት ተኝቶ መታከሚያ ከፍልን በጎበኘበት ወቅት፣ ተኝተው በመታከም ላይ ከነበሩት 20 ከፍተኛ የአዕምሮ ጭንቀት እና ድንጋጤ (trauma) ታካሚ ሕፃናት መካከል 16ቱ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው።

ከሕፃናቱ መካከል እጃቸውን፣ እግራቸውንና እና አይናቸውን ጨምሮ የአካላቸውን ክፍል ያጡ ወይም የተለያየ አይነት የአካል ጉዳት የደረሱባቸው የሚገኙ ሲሆን፣ በተለይ በሕፃናት ላይ ለደረሱት ጉዳቶች አንዱ ምክንያት በመሬት ውስጥ “የተቀበሩ እና በሜዳ ላይ የተጣሉ ፈንጂዎች” የሚደርስ ጉዳት ነው።

ትግራይ ክልል የመሰረታዊ ልማት፣ የማኅበራዊ እና የአስተዳደራዊ አገልግሎቶችን በአፋጣኝ የመመለሱ ተግባር ልዩ ትኩረት ይሻል ሲል ኮሚሽኑ አሳስቧል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮጵያዊያን
የካቲት 4 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *