የተናቀናጀ የጤና እና ልማት አገልግሎት ድርጅት የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ከኦሮሚያ ጤና ቢሮ ጋር በጋራ ለሶስት አመታት የሚተገብሩት ይሄ ፕሮጀክት 9 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦለታል፡፡
ይሄ የድጋፍ ስምምነት በዋናነት ለኤች አይ ቪ ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚውል ሲሆን በተለይ ህክምና ላቋረጡ ኤች አይ ቪ በደማቸው ላለ ታማሚዎችም ህክምና ይውላል ተብሏል፡፡ ቫይረሱ በደማቸው ኖሮ እንዳለባቸው ሳያውቁ የሚኖሩትን በዚህ ፕሮጀክት በስፋት ለመለየትም ታቅዷል፡፡
ኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ያለባቸውን ሰዎች በመለየት ሌሎች ለቫይረሱ የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመመርመር የጸረ ኤች አይ ቪ ኤድስ ህክምና እንዲጀምሩ ይደረጋልም ተብሏል። ይሄ ፕሮጀክት ቤተሰብና ማህበረሰብ ተኮር ነው የተባለ ሲሆን ራሱን ህብረተሰቡን በህክምና አሰጣጥ ሂደቱ ዋና ተዋናይ የማድረግ መንገድ ይከተላል ተብሏል፡፡
ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ ክልል በ41 ወረዳዎች እና ከተሞች ላይ እንደሚተገበር ፕሮጀክቱን ይፋ በማድረጊያ ስነ ስርአት ላይ የተጠቀሰ ሲሆን ድጋፉ በተለይ እድሜያቸው ከ9 እስከ 14 ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ይውላል ተብሏል።
የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መንግስቱ በቀለ እንደተናገሩት የኤች አይ ቪ ስርጭት መጠን በሀገራችን ከአመት አመት በተመሳሳይ መጠን ነው እየጨመረ ያለው፣ የስርጭት መጠኑ ባለበት የመሆኑን እውነታ ለመቀየር ነው ይሄ የድጋፍ ስምምነት ያስፈለገው ብለዋል፡፡
ድጋፉን ለታሰበለት አላማ በማዋል ፕሮጀክቱን ስኬታማ ማድረግ አለብን ያሉ ሲሆን ኤች አይ ቪ እንዳለባቸው ሳያውቁ እየኖሩ ካሉት 95 በመቶው እንዲያውቁ ማድረግ፣ ኤች አይ ቪ ኖሮባቸው ህክምና ከማያገኙት 95 በመቶው እንዲያገኙ ማድረግና ህክምና ላይ ካሉት ደግሞ 95 በመቶው ተሽሏቸው ውስጣቸው ያለው የቫይረስ መጠን ለሌሎች እንዳያስተላልፉ በሚያስችል ሁኔታ ማድረግን ግቡ ያደረገው የተመድ የ2030 ፤ 95-95-95 ግብ እውን እንዲሆን ይሄ ፕሮጀክት የበኩሉን መወጣት አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በሔኖክ አስራት
የካቲት 5 ቀን 2013 ዓ.ም











