በኢትዮጵያ 426 አይነት ጥቅም ላይ ሊውሉ የማይችሉ የፀረ ተባይ መድሃኒቶች መከማቸታቸው ተገለጸ።

በአያያዝ ጉድለት እና የመጠቀሚያ ጊዜ አልፎባቸው ከተከማቹ ኬሚካሎች ውስጥም 80 በመቶዎቹ አለመወገዳቸውን የፌዴራል መንግስት የግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታውቋል።

ኤጀንሲው በአዘጋጀው አውድ ጥናት ላይ እንደተገለጸው፣ በኢትዮጵያ የፀረ -ተባይ ኬሚካል ላብራቶሪ በሀገር ውስጥ ባለመኖሩ፤ በአያያዝ ምክንያቶች የሚበላሹ ፣ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው እና የእስቶኮልም ክልከላን በመጻረር ምክንያት ጥቅም ላይ ሊውሉ የማይችሉ በርካታ ፀረ – ተባይ ይገኛሉ ተብሏል ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኬሚስትሪ መምህር ዶክተር መስፍን ረዲ በአውደ ጥናቱ ላይ እንደገለጹት በኢትዮጵያ 426 ጥቅም ላይ ሊውሉ የማይችሉ ፀረ – ተባይ አሉ።

ይህ በመንግሥት ክምችት ብቻ ያለ ሲሆን በዝቅተኛ የእርሻ ስራ ያሉ እና በግለሰብ ደረጃ ያሉ 80 በመቶ አልተወገደም ብለዋል ዶክተር መስፍን።

በመንግስት ይሁን በግለሰብ ለተለያዩ አገልግሎት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የጸረ ተባይ እና ኬሚካሎች የጉዳትም ሆነ የጥቅም ሁኔታዎችን የሚያረጋገጥ ላብራቶሪ በኢትዮጵያ አለመኖሩንም ዶክተር መስፍን ተናግረዋል።

የፌዴራል መንግስት የግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሀጂ ኢብሳ በበኩላቸው ችግሩን መፍታት የሚያስችል ወጥ የሆነ ጥናት የለንም ብለዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም እና የኬሚካል ፍንዳታ እንደሌሎች ሀገር አይነት ችግር እንዳይገጥመን ጥናት ጀምረናልም ብለዋል ዳይሬክተሩ።

በዳንኤል መላኩ
የካቲት 8 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.