ኢትዮጵያ በኦጋዴን ተፋሰስ አገኘሁ ያለችው የተፈጥሮ ነዳጅ እስካሁን ለምን ዘገየ?

የቻይናው ፖሊ ጂሲኤል ፔትሮሊየም ኢንቨስትመንት የተሰኘው ኩባንያ በሶማሊ ክልል ሂላላ በተባለው ሥፍራ ያገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ 2010 ዓ.ም የሙከራ ምርት ማውጣት መጀመሩ ይታወሳል፡፡

በወቅቱም መንግስት ኢትዮጵያ በቀን 450 በርሜል ድፍድፍ የተፈጥሮ ጋዝን ማምረት እንደምትችል ተነግሮም ነበር፡፡

በዚህ ስፍራ ተገኘ የተባለው የነዳጅ መጠን እስከ 8 ትሪሊዮን ኪውቢክ ሜትር እንደሚደርስ ተገልጾ የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያ ነዳጁን ወደ ውጭ በመላክ በዓመት አስከ 8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደምታገኝም ለህዝብ ይፋ ሆኖ ነበር።

ይሁን እንጅ ይህ ተስፋ ሰጪ እቅድ ከተነገረ 3 አመታት ቢቆጠሩም ዛሬም ግን ወደ ምርት መግባት እና አገሪቱን ተጠቃሚ ማድረግ አልተቻለም፡፡

ለመሆኑ ኢትዮጵያ አገኘሁት ያለችዉ የተፈጥሮ ጋዝ ከምን ደረሰ? የነዳጅ ማስተላለፊያዉ እና የሌሎች መሰረተ ልማቶች ግንባታስ ጉዳይ ምን ላይ ይገኛል? ስንል ኢትዮ ኤፍ ኤም የሚመለከተዉን አካል ጠይቀናል፡፡

የማዕድን እና ኢነርጅ ሚኒስትር ዴኤታ እና የነዳጅ ዘርፍ ሀላፊ ዶክተር ኳንግ ቱትላን ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት የቅድመ ዝግጅት ስራዎቹ ከነዳጅ አዉጪ ኩባንያዉ ጋር እየተሰራ ነዉ ብለዋል፡፡

የቅድመ ዝግጅ ስራዉ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? ለምንስ ነዉ ዘገየዉ? ኩባንያውን የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር በፍጥነት ወደ ስራ ለማስገባት ምን እየሰራ ነዉ? ብለን ላነሳነዉ ጥያቄም ስራዉን የተረከበዉ የፖሊ ጂሲ ኤል ኩባንያ ለ 36 ወራት ነበር ብለዋል።

መንግስት ለኩባንያው ተገቢውን ድጋፍ እያደረገ ቢሆንም ነዳጅ የማውጣት ስራው መዘግየቱ የእኛም ጥያቄ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል።

የፖሊ ጂሲ ኤልን ኩባንያ የአስተዳደር ሃላፊ ዣንግ ካንጂ በበኩላቸው የነዳጅ ማውጣት ስራው የዘገየው የበጀት እጥረት ስለገጠመን ነዉ ብለዋል።

የበጀት ችግሩን ለመፍታትም ሌሎች የቢዝነስ አማራጮችን እየጠበቅን እንገኛለን ያሉት ሃላፊው ምናልባትም በጀቱን እስከ ሃምሌ 2013 ዓ.ም ድረስ እናገኛለን ብለን እናስባለን ከዚያን በኋላ ወደ ስራ እንገባለን ብለዉናል፡፡

በርካታ ባለሙያዎች እንደሚሉት ግን ኢትዮጵያ ላለፉት 70 አመታት ያባከነችዉን ጊዜ አሁንም እንደቀጠለ ነዉ ይላሉ፡፡

አቶ ያሬድ ሃይለመስቀል የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ሲሆኑ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ የነዳጅ ጉዳይ ከንጉሱ እና ከደርግ የአስተዳደር ጊዜ ጀምሮ የሚወራ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ግን አሁንም ድረስ አለ ከተባለው ነዳጅ ምንም ያገኘችዉ ነገር የለም ለዚህ ደግሞ ዋነኛዉ ምክንያት የመንግስት ቸለተኝነት እና የፖሊሲ አተገባበር ችግር እንደሆነ አንስተዋል፡፡፡

የነዳጅ ሀብት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የእድገት ጎዳና እንደሚያሻግራት ቢታመንም አገሪቱ ከዘርፉ አንዳች ነገር ሳታገኝ የነዳጅ ዋጋዉ እያሽቆለቆለ ይገኛል።

ስለዚህ መንግስት ከተለመደዉ አሰራር ወጥቶ በትኩረት መስራት እንዳለበትም አቶ ያሬድ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በየዓመቱ በአማካኝ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ከውጭ አገራት ነዳጅ ገዝታ በማስገባት ላይ ትገኛለች።

በአባቱ መረቀ
የካቲት 11 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *