መንግስት ከመጋቢት ጀምሮ ነዳጅን በዱቤ መግዛት እንዲቀር በሚል ያስተላለፈው ውሳኔ እንዲዘገይለት የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማህበር ጠየቀ።

መንግስት በንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚንስቴር በኩል ከመጋቢት 1 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ነዳጅ በዱቤ ይወስዱ የነበረውን አሰራር እንዲቀር መወሰኑ ይታወሳል።

የነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች ከመንግስት በዱቤ የሚቀበሉት ነዳጅ ከመጋቢት አንድ ጀምሮ በተዋረድ አየቀነሰ በሚቀጥለው አመት ደግሞ ሙሉ ለሙሉ አንዲቀረ ሆኖ በመታቀዱ ነዳጅ አዳዮች ከነዳጅ አቅራቢዎች በዱቤ አንዳይቀበሉ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማህበር ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ውሳኔው እኛ በውይይቱ ላይ ባልተገኘንበት ነው የተካሄደው ብሏል።

ነዳጅን በቀጥታ ለሸማቹ ማህበረሰብ የምሸጠው እኛ ሆነን ሳለ በውይይቱ ላይ ሳንጋበዝ አቅማችን ሳይታይ መወሰኑ አግባብ አይደለም ብለዋል የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ሔኖክ መኮንን።

የነዳጅ ግብይቱ ከዱቤ ወጥቶ በካሽ መካሄዱን እንደግፋለን የሚሉት ሊቀመንበሩ ጥያቄያችን የዝግጅት ጊዜ ይሰጠን ነው ብለዋል።

ነዳጅ በዱቤ ስንቸረችር ከርመን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ካሽ ሽያጭ ግቡ ስንባል ጊዜ ያስፈልገናል የምንዘጋጅበት ተጨማሪ ጊዜ ይፈቀድልን ሲሉ መንግስትን ጠይቀዋል።

ሊቀመንበሩ አክለውም አሁን አንድ ሌትር ሸጠን ከምናገኘው 23 ሳንቲም ወደ 80 ሳንቲም ከፍ አንዲልላቸውም ጠይቀዋል።

መንግስት ከነዳጅ ትርፍ ባታገኙም ከመኪና ዘይት ትርፍ ታገኛላቹ ቢልም ዘይት አከፋፋይ ኩባንያዎች የመኪና ዘይቱ በየኪዎስኩ እንዲከፋፈል በማድረጋቸው ፍትሀዊ እና በውድድር ላይ ያልተመሰረተ ንግድ እየተካሄደ በመሆኑ ከውድድር እንድንወጣ እየተደረግን ነው መንግስት ህግ ያስከብር ሲሉም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማህበር በ1960ዎቹ የተቋቋመ ሲሆን አሁን ላይ ከ120 በላይ ነዳጅ አዳዮችን በአባልነት አቅፏል።

በኢትዮጵያ አንድ ሺህ የነዳጅ ማደያዎች በስራ ላይ እንዳሉ ከማህበሩ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

በሳሙኤል አባተ
የካቲት 12 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.