የሀገር ውስጥ ዜና

ከአንድ ወር በፊት መተግበር የጀመረው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ስምምነት ኢትዮጵያን ይጠቅም ይሆን?

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ዞን የአፍሪካ አገራት ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነጻ በሆነ መንገድ ወደ ገበያ አንዲያቀርቡ እና የእርስ በርስ የንግድ ትስስርን ለማሳደግ ያለመ የንግድ ስምምነት ነው።

ይሄንን የአፍሪካ ነጻ የንግድ ዞንን ማቋቋም አስፈላጊ ነው በሚል እስከሁን ሀገራችንን ጨምሮ 34 የአፍሪካ ሀገራት ስምምነቱን መቀበላቸው ይታዎሳል፡፡

ስምምነቱ እ.ኤ.አ በ2018 የተጀመረ ሲሆን፤ የጋራ የመገበያያ ገንዘብና ቪዛ ያለው በመሆኑ ወደ 1.3 ቢሊዮን ሕዝብን በንግድ ያስተሳስራል ተብሏል፡፡

ሀገራችን በነጻ ንግድ ቀጠናው አባል መሆኗ ሊኖራት የሚችለውን ተጠቃሚነትና በተለይ ደግሞ የበለጠ ተጠቃሚ ልሆንባቸው የምንችልባቸው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎቻችን የትኞቹ ናቸው? ስንል የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችን ጠይቀናል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም (107.8) ካነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች መካከል ኢንጅነር አለማየሁ ንጋቱ አንዱ ናቸው፡፡

ባለሙያው እንደሚሉት ከሆነ ይህ አይነት የንግድ ስምምነት ድንበር የማያግደው የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግበት በመሆኑ፣ የአስመጪዎችን ቀረጥ በመቀነስ ነጻ ዝውውርን ያበረታታል፤ ለአነስተኛና መካከለኛ ተቋማት፣ በተለይ ለሴቶች እንዲሁም ለወጣቶች የስራ እድልን ይፈጥራል፤ በርካታ የገበያ አማራጮችን ለማግኘት ያስችላል፤ የተሳታፊውን ዘርፍ ገቢ ይጨምራል፣ ሕገወጥ ንግድ እንቅስቃሴን ይቀንሳል፣ ግብር ከፋይነትን ይጨምራል፣ የሰው ሃይልን ለመሸጥ (Export) ያስችላል፣ ብለዋል፡፡

ሌላኛው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አቶ ዋሲሁን በላይ በበኩላቸው፤ በነጻ ንግድ ቀጠናው የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን፤ በመጀመሪያ በዚሁ የንግድ እንቅስቃሴ አይነት ተጠቃሚ ሊያደርጉን የሚችሉትን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎቻችንን መለየት ይኖርበናል ይላሉ፡፡

በዚህም አየር መንገዳችን በአፍሪካ ተጽእኖ ያለው በመሆኑ በዘርፉ በትጋት ቢሰራበት በቀጠናው እጅግ ውጤታማ ያደርገናል ብለዋል፡፡

ባለሙያው አክለውም የመካከለኛና አነስተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎቻችን፤ ያሉንን ጥሬ እቃዎች በመጠቀም አንዲያመርቱ በማድረግና ለገበያው ማቅረብ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

በሀገራችን የቡና፤ የቆዳና ሌጦ፤ የሰሊጥ፤ የጥጥና ሌሎችም በርካታ የጥሬ እቃዎችና የኢንዱስትሪ ግብአቶች ያለን መሆኑን ያነሱት ባለሙያው፤ ጥሬ እቃዎቻንን ከመላክ ይልቅ ወደ ምርት ቀይረን ለመላክ መጣር ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ይህ ካልሆነ ግን ይላሉ ባለሙያው፤ የውጪ ሀገራት ምርቶች ማራገፊያ ልሆን እንችላለን ብለዋል፡፡

እንደ ባለሙያው ሀሳብ ከሆነ በአፍሪካ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ፤ ብዙዎቹ የአፍሪካ ሀገራት በተቀራራቢ የኢኮኖሚ እድገት ላይ መሆናቸው፤ የትራንስፖርት እና የቪዛ ጉዳዮች፤ የድንበር ውዝግቦች፤የቴክኖሎጂና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶችም ይህንን የንግድ እንቅስቃሴ በትክክል ለማከናዎን እንቅፋቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ አብራርተዋል፡፡

ስለሆንም እነዚህንና መሰል ችግሮችን በመለየት እንዲሁም የሚስተካከሉበትን አማራጭ ሃገራት በመመካከር ጥቅሞቻቸውን ማስጠበቅ እንዳለባቸው ባለሙያዎቹ አሳስበዋል፡፡

ከአንድ ወር በፊት መተግበር የጀመረው የአፍሪካ ነጻ ንግድ ስምምነት የአፍሪካ የንግድ ልውውጥ መጠንን አሁን ካለበት 16 በመቶ ወደ 33 በመቶ እንደሚያሳድገው ይጠበቃል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
በጅብሪል መሀመድ
የካቲት 16 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *