ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ላይ ተወዳዳሪ አምራቾችን ካልፈጠረች የአገራት ሸቀጦች ማራገፊያ ልትሆን ትችላለች ተባለ።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እንዳስታወቀው አገሪቱ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ተግባራዊ ከማድረጓ በፊት የንግዱ ማህረሰብን ብቁ ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከፓን አፍሪካን ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ጋር በመተባበር የነፃ የንግድ ቀጠናው በሚኖረው ስጋትና ጠቀሜታ ዙሪያ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በአዲስ አበባ እየመከረ ነው።

በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጂነር መልዓኩ አዘዘው እንደገለፁት የአፍሪካን አህጉራዊ የንግድ ቀጠና ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት አምራች ድርጅቶችን ብቁና ተወዳዳሪ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በርካታ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ ለንግዱ ማህበረሰብ አትራፊ አይደለም ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ እነዚህ ችግሮች እስካልተፈቱ ድረስ የነፃ የንግድ ቀጠናው አዋጭ እንደማይሆን አንስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በአገሪቱ ብቁ ነጋዴዎች ፣አለመኖር፣ የጥሬ እቃ አቅርቦት ችግር፣ ቴክኖሎጂ ክፍተት እና ጥራት ያለው ምርት አለመኖር ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ተወዳዳሪ እንዳትሆን ያደርጋታል ብለዋል ኢንጂነር መልዓኩ።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና የገበያ አማራጮችን ከማስፋት አኳያ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ቢታወቅም ኢትዮጵያን የዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ የንግድ ማህረቡን ማንቃት ያስፈልጋልም ተብሏል ።

የኢትዮጵያ የንግድ ማህበረሰብ የተለያዩ ምርቶችን በአገር ውስጥ ከማምረት ይልቅ ከውጭ አገራት ማስገባትን ይመርጣሉ ፣ይህ ደግሞ አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲገጥመት ያደርጋል ።

ኢትዮጵያ ከሰሞኑ ከዩክሬን እንቁላል ልታስገባ መሆኑም የችግሩ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ተነስቷል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና በቅርቡ በይፋ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል ።

በአባቱ መረቀ
የካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *