የዩክሬን ብዙሃን መገናኛ በትናንትናው ዕለት አገራቸው ወደ ኢትዮጵያ እንቁላል መላክ ልትጀምር መሆኑን የሚገልጽ ዘገባ ከተሰራጨ በኋላ ጉዳዩ የብዙዎችን ትኩረትን ስቧል።
ኢትዮ ኤፍ ኤም ለመሆኑ የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎች እና አቀናባሪዎች ማህበር በዚህ ዜና ላይ ምን ይላል ስንል ጠይቋል።
የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሀኑ ሚሊዮን የኮሮና ቫይረስ ባስከተለው ጉዳት ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የዶሮ ጫጩቶች ተደፍተዋል ብለዋል።
መንግስት ለሆቴሎች እና ተያያዥ ሙያ ውስጥ ላሉ የኢንቨሰትመንት ስራዎች ያደረገውን ድጋፍ ለዶሮ አርቢዎች እና አቀናባሪዎችም ድጋፍ እንዲያደርግ ቢጠየቅም ምላሽ አልሰጠንም ብለዋል ስራ አስኪያጁ።
ዶሮ አርቢዎች እና ስጋ አቀናባሪዎች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የገበያ እጥረት ሲያጋጥማቸው የግድ ምርቶቹን እንዲያቃጥሉ አስገድዷቸዋል በርካቶችም ከስረው ከስራው ወጥተዋል ብለዋል።
በመሆኑም አሁን ላይ ሆቴሎች እና ፋብሪካዎች ወደ ስራ ሲመለሱ የእንቁላል እና የዶሮ ስጋ ምርቶች እጥረት ማጋጠሙ እርግጥ ነው ብለዋል።
እንቁላል በቀላል ነገር ማምረት የሚቻል ግን ጥቅሙ እጅግ ብዙ የሆነ ስራ ነው የሚሉት ስራ አስኪያጁ መንግስት ለዚህ ዘርፍ ትኩረት ባለማድረጉ የምግብ ዋስትና፣የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፤የዜጎች ስራ አድል ፈጠራ እና ሌሎች ብዙ ጉዳቶችን እያስተናገደ ነውም ብለዋል።
እንቁላል ከዩክሬን ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ የትኛው የመንግስት ተቋም እንደተነጋገረ አላወኩም ያሉን አቶ ብርሀኑ ለዘርፉ ትኩረት ባልተሰጠበት ሁኔታ ይህ ቢሆን አይገርምም ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የዶሮ ስጋ፤የዳክዬ ስጋ እና ተርኪ የሚሰኙ ከዶሮ ስጋ ጋር በተያያዘ ከተለያዩ የአለማችን አገራት ስታስገባ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረች ሲሆን አሁን ደግሞ እንቁላል ልታስገባ ነው መባሉ ብዙዎችን አስቆጥቷል።
በሳሙኤል አባተ
የካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም











