ኢትዮጵያ እርቅን ከውጭ ለማስገባት መሞከሯን እንድታቆም ምሁራን አሳሰቡ።

ዕርቅ ከውጭ ለማስገባት መሞከራችንን ማቆም አለብን ፣ ዕርቅ ጠይቀን ግጭት ሲላክልን ነው የኖርነው ብለዋል ለኢትዮ ኤፍ ኤም ሀሳባቸውን የሰጡ ምሁራን።

እውነተኛ ይቅርታና የግጭት መፍትሄ የሚገኘው ከኢትዮጵያዊ ዕርቅ ነው፣ የአድዋ ድል የተገኘው ዕርቁ ከውስጥ ስለሆነ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ከሶስት ቀን በኋላ የአድዋ በዓል ይከበራል፤ ነገሩ የካቲት ወሩን ሙሉ ነው ዘንድሮ የተከበረው፤ ወሩን ሙሉ እናክብር ሲባል ምን እያደረግን ነው ማክበር ያለብን የሚለው ጉዳይ በተለያዩ መድረኮች ተነስቶ ለውይይት ቀርቧል፡፡

አሁን ካለንበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር አድዋን ትርጉም ባለው መንገድ አከበርን የሚባለው ግጭት ሊፈጥሩ የሚችሉ ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን ብለን ስንታረቅ ነው ብለዋል ምሁራኑ፡፡

ዶ/ር ሳሙኤል ተፈራ በሰላም ሚኒስቴር ውስጥ የሚኒስትሯ የፖሊሲ አማካሪ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና እስያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ የአድዋ ድል የእርቅ ገፅታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የአደዋ ጀግኖቻችን ቂም ቁርሾዎቻቸውን ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ብለው፣ በአንድነት በመቆም ነው ያንን አንፀባራቂ ድል ያስመዘገቡት ሲሉ ለድሉ መገኘት ልዩነትን ማስታረቅ ፋይዳውን ተናግረዋል፡፡

ስለ ዕርቅ ለመነጋገርና ሰላምን ለመስበክ ደግሞ ካሁን የተሻለ ጊዜ የለም ሲሉ አጣዳፊነቱን ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህርና የህግ ብዝሀነት ተመራማሪ ዶ/ር ካይረዲን ተዘራ በዕለቱ የዕርቁን መላና ጥበብ ከውጪ ሳይሆን ከራሳችን ውስጥ እንፈልግ ያሉ ሲሆን እነዚህን በውስጣችን ያሉ፤ እሴቶችን እያወጣን መነጋገር አለብን ብለዋል፡፡

የሚያስተሳስረን ብዙ ነው የሚሉት ዶ/ር ካይረዲን ሁላችንም የሚያስታርቀን ላይ ትኩረት አድርገን እንድንነጋገር እና እንድንቀሳቀስ ምሁራኑ ሲሉ መክረዋል፡፡

ዕርቅ ከውጭ ለማስገባት መሞከራችንን ማቆም አለብን ፣ ዕርቅ ጠይቀን ግጭት ሲላክልን ስለኖርን ከስህተታችን ልንማር ይገባል፤ መፍትሄው ኢትዮጵያዊ ዕርቅ ነው ብለዋል ምሁራኑ።

በሔኖክ አስራት
የካቲት 19 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.