መንግስት በኮሮና ቫይረስ ታመው ወደ ጽኑ ሕክምና ለሚገቡ ለእያንዳንዳቸው ቢያንስ 200 ሺህ ብር ወጪ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታወቀ።

በኮሮና ቫይረስ የተያዘ አንድ ሰው በአማካኝ በአንድ የፅኑ ህክምና ማሽን ላይ ለመቆየት ሲገደድ እስከ 9 ያክል ቀናት እንደሚቆይም ተነግሯል፡፡

ይህ ሁኔታ አልፎ አልፎ ከ10 -20 ቀናት ያክል የሚከሰት ሲሆን በዚህም ለፅኑ ህሙማን መርጃ የሚያገለግለው ይህ የማሽን አልጋ የሚያሶጣው ወጪ አሳሳቢ እንደሆነ ኢትዮ ኤፍ ኤም ከጤና ሚኒስቴር ሰምቷል፡፡

በጤና ሚኒስትር የክሊኒካል ሰርቪስ ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ ሰማን ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት በአሁኑ ሰዓት የመተንፈሻ ማሽን የሚፈልጉ ፅኑ ህሙማን በአማካኝ ከ 9 ቀን እስከ 20 ቀን ድረስ በዚህ ማሽን ላይ ይቆያሉ።

አንድ በኮሮና ቫይረስ ተጠቅቶ ይህ ማሽን የሚያስፈልገው ሰውም በአማካኝ ለሳምንት ያክል ጊዜ ሲቆይ እስከ 200 ሺህ ብር ወጪ ያስወጣል።

ታካሚው ለሁለት ሳምንታትና ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ ሲቆይ ደግሞ 500 ሺህ ብርና ከዛ በላይ የሆነ ወጪን እንደሚጠይቅ ሰምተናል፡፡

መንግስት በእርዳታና ከራሱ ካዝና ሙሉ በሙሉ የህክምና ወጪውን በመሸፈን ለህብረተሰብ አገልግሎቱን እየሰጠ በሚገኘው በዚሁ በኮሮና ቫይረስ የማገገሚያ አገልግሎትም እየወጣ ያለው ወጪ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩ ተነግሯል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ ለፅኑ ክህምና አገልግሎት የሚረዱ ወይንም (ቬብትሌት) ማድረግ የሚችሉ የማሽን አልጋዎች 65 ብቻ ናቸው፡፡

በዚህም በአዲስ አበባ ለፅኑ ህሙማን የኮሮና ቫይረስ ታካሚዎች ህክምና መስጠት የሚችሉ የማሽን አልጋዎች ሙሉ በሙሉ መያዛቸውን ሰምተናል።

በሃገሪቱ በአጠቃላይ ወደ 645 የፅኑ ህሙማን (የማሽን አልጋዎች) እንዳሉ የነገሩን አቶ ያእቆብ በሃገሪቱ የሚገኙ የኦክስጅን አልጋዎች እጥረት እያጋጠመ ባይሆንም ማሽን የሚፈልጉ የፅኑ ህሙማን አልጋዎች ግን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ብለውናል፡፡

በዚህም ማሽን የሚፈልጉ የፅኑ ህሙማን አልጋዎች ወጪያቸውም ሆነ የቁጥራቸው ማነስ ሁኔታውን በጣም አስቸጋሪ እንደሚያደርገውም ተናግረዋል።

በየውልሰው ገዝሙ
የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.