አዲስ አበባ ሲልክ ሮድ ጠቅላላ ሆስፒታል የዉጭ አገር የህክምና ጉዞን የሚያስቀር የህክምና አገልግሎት ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ፡፡

ሆስፒታሉ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቀዉ ከዚህ ቀደም ለህክምና አገልግሎት ወደ ታይላንድ፣ ህንድና ወደ ሌሎች አገራት ይሄዱ የነበሩ ህሙማንን የሚያስፈልጋቸዉን ህክምና እዚሁ እንዲያገኙ ለመስጠት በዝግጅት ላይ እገኛለሁ ብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ሲልክ ሮድ ጠቅላላ ሆስፒታል ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ፍራንክ ሊ ፍራንክ እንዳሉት፤ ህሙማን ወደ ዉጭ አገራት መሄድ ሳይጠበቅባቸዉ በአገር ዉስጥ ህክምና የሚያገኙበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡

በኢትዮጵያ ዉስጥ የማይሰጡ የጭንቅላት፤ ህብረ ሰረሰር ህክምናን ጨምሮ ሌሎች ከባድ ቀዶ ጥገናዎችን ሆስፒታሉ እንደሚሰጥም ሃላፊዉ አስታዉቀዋል፡፡

በቅርቡም ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር በጋራ በመሆን ለ6 ህሙማን የህብረ ሰረሰር ቀዶ ጥገና ህክምና መስጠቱን ስራ አስኪያጁ አንስተዋል፡፡

ሆስፒታሉ ከተከፈተ 11 ወራትን ቢያስቆጥርም በኮቪድ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ አለመግባቱ የተነገረ ሲሆን አሁን ላይ ግን ወደ ስራ ለመግባት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ሰምተናል፡፡

የህክምና ማዕከሉ የኮቪድ 19 ህሙማንን ተቀብሎ የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን የኮቪድ ምርመራ እንዲያደርግም ከጤና ሚኒስቴር እዉቅና አግኝቷል፡፡

የሲልክ ሮድ ሆስፒታል የዉጭ ምንዛሬን ችግር ከማስቀረቱም በተጨማሪ ለበርካታ ኢትጵያዉያን የስራ እድል እንደፈጠረም ተገልጧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የአየር አምቡላንስ በመስጠጥ ከተለያዩ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ለሚመጡ ህሙማን የሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጥም ታዉቋል፡፡

አብዛኛዉ ህክምናዎች ከዉጭ አገር በመጡ ስፔሻሊስቶች እንደሚሰጡ ያስታቁት ዶክተር ፍራንክ ሊ ፍራንክ ሆሰፒታሉን ለመገንባት 30 ሚሊዮን ዶላር እንደፈጀም አስታዉሰዋል፡፡

በአባቱ መረቀ
የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *