በምስራቅ አፍሪካ ታላቁ የውሃ ጋን የሆነው ጮቄ ተራራን ከጥፋት ለመታደግ ጠንካራ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ምሁራን አሳስበዋል፡፡

የጮቄ ሰንሰለታማ ተራራ በምስራቅ ጎጃም ዞን ስናን ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ከባህር ጠለል በላይ 4 ሺ 100 ከፍታ ያለውና 7 ሺህ ሄክታር ቦታን ይሸፍናል፡፡

ተራራው ከ270 በላይ ምንጮችና ከ50 በላይ ለሚሆኑ ወንዞች ደግሞ መፍለቂ በመሆኑ በምስራቅ አፍሪካ ታላቁ የውሃ ማማ በመባል ይታወቃል፡፡

የጮቄን ተራራ ልዩ የሚያደርው ደግሞ በውስጡ ከሚፈልቁት 54 ወንዞች አብዛኛዎቹ የአባይ ወንዝ ገባር ወንዞች መሆናቸው ነው፡፡

አሁን ላይ ግን በአካባባው ህገ ወጥ ሰፈራና ልቅ ግጦሽ እየተስፋፋ በመምጣቱ፤ ተራውው ጉዳት እየደረሰበት መሆኑ ተገልጿል፡፡

የተራራው አደጋ ላይ መሆን ደግሞ በአባይ ወንዝ ላይ ብሎም በህዳሴው ግድብ ላይ ቀጥተኛ ተፅእኖ እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡

ከሰሞኑ የአዲስ አበባ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በ45 ዩኒቨርሲዎች መካከል ጮቄን በጋራ ለማልማትና ለመጠበቅ የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም በጮቄ ተራራ ላይ ከ20 አመት በላይ ጥናት ካደረጉትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪ ከሆኑት፤ ከፕሮፌሰር በላይ ሰምአኔ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም:- የጮቄ ተራራ አጠቃላይ ገጽታው ምን ይመስላል?

ፕሮፌሰር በላይ:- ጮቄ በኢትዮጵያ ካሉ ከፍተኛ ቦታዎች የሚመደብ በመሆኑ የበርካታ የዓባይ ገባር ወንዞች መነሻ ነው፤ የኢትዮጵያን የአየር ጸባይ የሚወስን ነው፤ የበርካታ ሀገር በቀልና ለመድሃኒትነት የሚያገለግሉ እጽዋት መብቀያ ነው፤ የተለያዩ አዝእርት ማምረቻ ነው፤ የብዝሀ ህይወት መጠጊያ ነው፤ በተለይ ደግሞ የህዳሴውን ግድብ ህልውና የሚወስን ቢሆንም ነገር ግን አሁን ላይ ተራራው ለአደጋ ተጋልጧል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም:- የጮቄ ስምምነት አካባቢውን በማልማቱ በኩል ምን ሚና ይኖረዋል?

ፕሮፌሰር በላይ:- በመጀመሪያ አካባቢው ለህዳሴው ግድብና ለኢትዮጵያ ምን ያህል ወሳኝ ቦታ እንደሆነ ግንዛቤን ይፈጥራል፡፡
ይህም ዩኒቨርሲቲዎች ከሌሎች ተቋማት ጋር አካባቢውን ለማልማት በትብብር እንዲሰሩ እድልን ይፈጥራል፤ ወደፊትም ወቅቱን የጠበቀ የምሁራን ምክክር እንዲደረግና ስራዎችን ወደ ተግባር ለመቀየር ያስችላል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም:- ጮቄን ማልማት የኢትዮጵያውያን አቅም ብቻ በቂ ነውን? የተፋሰሱ ሀገራትስ በተለይ በዓባይ ወንዝ ላይ የበለጠ ተጠቃሚ የሆኑት ሱዳንና ግብጽን በልማቱ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማድረግ ምን ተሰርቷል?

ፕሮፌሰር በላይ:- አካባበውን በማልማት የአባይ ወንዝ ተፋሰስን ከመነሻው ማጎልበት እንደሚቻል አስታውቀን፤ ሀገራቱ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀናል፡፡
ከዚህ በፊትም ፖሊሲዎችንና አጀንዳዎችን በማዘጋጀት አቅርበናል፤ ምላሻቸውን እየጠበቅን ነው፡፡

የጮቄን ተራራ በማልማትና ወደ ነበረበት ይዞታው በመመለስ፤ የዓባይ ወንዝን ተፋስስ ማጎልበት እንደሚቻል ያስረዱት ተመራማሪው፤ በተቃራቂው ደግሞ አካባቢው የማይለማና ጥበቃ የማይደረግለት ከሆነ፤ የዓባይ ወንዝም ሆነ የታላቁ ህዳሴው ግድብ፤ ችግር ውስጥ የሚገባ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም ነው ያሉት፡፡

ስለሆነም አካባቢውን ማልማት ማለት የህዳሴውን ግድብ ከጉዳት መታደግ በመሆኑ፤ የሁሉም አካላትን ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን ተመራማሪው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በጅብሪል ሙሃመድ
የካቲት 30 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.